
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባንቻየሁ ተፈራ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ስትኾን የሀገር አቀፉ አንድነት የቤት ሠራተኞች ማኅበር ኅብረት ደግሞ ጸሐፊ ናት። ወላጆቿ በሕጻንነቷ ስለሞቱባት ገና በ10 ዓመቷ ከቤተሰቦቿ እርቃ በቤት ሠራተኝነት ህይዎትን በጎንደር እንደጀመረች ትናገራለች። ትምህርቷን በአሠሪዎቿ ፈቃድ በማታው ፕርግራም ብታጋምስም እንቅፋት ገጠማት፤ እናም አቋረጠችው። በዚያ ላይ ደግሞ ልጅ ወለደች።
ችግር ሲበረታባት ወደ ትውልድ ሀገሯ መመለስ ብትፈልግም ወላጆቿ ስለሞቱ መግቢያ የላትምና ወደ ባሕር ዳር አቀናች። በሰዎች ቤት በተመላላሽ እየሠራች ያቋረጠችውን ትምህርቷን ቀጠለች። ለልጅ ማሳደጊያ እና ለትምህርት ክፍያ እንዲኾናት መንገድ ዳር ችፕስ ስትሸጥ ያገኘቻት ጋዜጠኛ ማኅበር ለማቋቋም ከተዘጋጁ የቤት ሠራተኞች ጋር አገናኘቻት። ”የባሕር ዳሩን የቤት ሠራተኞች ማኅበር 40 ኾነን አቋቋምነው” ብላለች።
እነ ባንቻየሁ ባሕር ዳር ላይ ይሠባሠቡ እንጂ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ጥንስሱ ከወደ ደብረ ማርቆስ በ2002 ዓ.ም እንደኾነ ገልጻለች። በወቅቱ አንዲት የበጎ አድራጊ ድርጅት ሠራተኛ የቤት ሠራተኞችን ችግር አይታ ማኅበር እንዲያቋቁሙ እንዳደረገችም ይነገራል። አሁን ላይ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበራት ኅብረት 52 ቅርንጫፍ ማኅበራት እና 12 ሺህ 580 አባላት አሉት። ”አንድነት የቤት ሠራተኞች ማኅበር” በሚል ስያሜ የተቋቋመው ሀገራዊ ማኅበር አባልም ናት።
ባንቻየሁ እና መሰሎቿ የማኅበራዊም ኾነ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ አይደሉም። የዓመት፣ የወሊድ ፈቃድ እና የበዓል እረፍት፣ የደኅንነት ዋስትና እንዲሁም ጡረታ የላቸውም። የወንድ ጓደኛ እንዲኖራቸው አይፈቀድም። የተለያዩ ጉዳቶችን ማስተናገድም ተለምዷል። ሃብት እና ጥቅማቸው በአሠሪው በጎ ፈቃድ ብቻ የተወሰነ ነው። በጥቅሉ ”የቤት ሠራተኞችን እንደ ሰው እኩል ያለማየት ልማድ ሰፍኗል” ነው ያለችው።
በአንጻሩም ”አንዳንድ የቤት ሠራተኞችም ችግር ሲፈጥሩ እየታየ መኾኑን” ጠቅሳለች። በቤት ሠራተኞች ላይ ለሚደርሱ እንግልቶች አንዱ ምክንያት ለቤት ሠራተኞች እና አሠሪዎቻቸው ግንኙነት የወጣ ሕግ ባለመኖሩ መኾኑ እየተጠቀሰ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት የወጣው የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 የቤት ሠራተኞችን ጉዳይ የተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል ብሎ ነው ያለፈው። ስለዚህ አዋጁ መብታችን በበቂው እንዳልሸፈነልን ነው የተረዳነው ብላለች ባንቻየሁ።
ስለኾነም ማኅበራቶቻቸው እና አባላቶቻቸውን ከአሠሪዎቻቸው ጋር የሚዋዋሉበት፣ መብታቸውን አስከብረው ግዴታቸውን የሚወጡበት ዝርዝር ሕግ እንዲወጣላቸው እየጠየቁ መኾኑን ነው ባንቻየሁ የገለጸችው። ዓለም አቀፍ ድንጋጌ 189 የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ አድርጎት ማየትም የማኅበራቸው የረጂም ጊዜ ግብ ነው።
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምክር፣ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር እሸቱ አለነ የቤት ሠራተኞችን መብት ለማስከበር ሕግ መውጣት እንዳለበት የተወካዮች ምክር ቤትም አምኖበት በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 56/2011 መደንገጉን ገልጸዋል። በቤት ውስጥ የሚሠሩ የቤት ሠራተኞችን ታሳቢ ያደረገ የ1952ቱ የፍትሐ ብሔር ሕግም የሠራተኛን ግንኙነት እና አያያዝ ለመደንገግ ያመላከታቸው እንዳሉ ጠቅሰው ነገር ግን ለአሁኑ ጊዜ በሚመጥን ደረጃ ሕግ የማውጣቱን ተገቢነት ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ መደበኛው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ድንጋጌም ሙሉ በሙሉ በቤት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ ሊኾን እንደማይችል ገልጸዋል። በአዋጁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚያወጣ ስለተመላከተ ከፌዴራሉ ሕግ አውጪ ፈቃድ ሳያገኙ ሌሎች አካላት በዚህ ላይ መመሪያም ኾነ ደንብ ማውጣት እንደማይችሉ ነው የገለጹት።
ይሁን እና የቤት ሠራተኞች የሚደርስባቸው በደል እስካለ ድረስ በመደበኛው የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ሕግ የሚገለገሉበት ሁኔታ ዝግ አለመኾኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በሌሎች ሕጎች የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል። እረፍት ስለመስጠት፣ በህመም እና በችግር ጊዜ ስለማባረር፣ ደመወዝን ስለመክፈል እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የተለየ ሕግ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ነው የሕግ ባለሙያው የተናገሩት። በተጨማሪም የቤት ሠራተኞች ከአሠሪዎቻቸው ጋር በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውል በጽሑፍ መያዝ እንደሚገባቸውም መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
