
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል። እቅዱን ለማሳካትም 8 ነጥብ 05 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል።
👉 ለመኾኑ የተገዛው ግብዓት ለምን ያህል አርሶ አደሮች ተደራሽ እየተደረገ ነው?
አርሶ አደር ማንዴ መኳንንት የፎገራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ እንደገለጹልን በየዓመቱ በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ሰብል ያመርታሉ። ለዚህም 10 ኩንታል ማዳበሪያ እጠቀማለሁ ነው ያሉት። በዚህ ዓመትም ከ2 ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለመሸፈን እየሠሩ ይገኛሉ። ከ10 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለመጠቀምም አቅደዋል። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ማግኘት የቻሉት ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ ነው።
በ2015/16 የምርት ዘመን በቂ ግብዓት ባለመቅረቡ የምርት መቀነስ እንዳጋጠማቸው ያነሱት አርሶ አደር ማንዴ በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥማቸው መንግሥት የዘር ወቅት ከመድረሱ ቀድሞ በቂ ግብዓት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። አርሶ አደር ማንዴ አሁን ላይ ማሳቸውን የማለስለስ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነግረውናል።
በ2016/17 የምርት ዘመን ግዥ ከተፈጸመው 8 ነጥብ 05 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደብ ላይ መድረሱን በምክትል ርእስ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታሉ ደግሞ ወደ ዩኒየኖች ገብቷል፤ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ አርሶ አደሮች እጅ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይ እንደ በቆሎ የመሳሰሉ ሰብሎችን ቀድመው ዘር በሚጀምሩ እንደ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ቀድሞ የማስገባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ይሁን እንጅ በአንዳንድ አካባቢዎች በዩኒየኖች የቀረበውን ግብዓት በትራንስፖርት እጥረት ወደ መሠረታዊ ማኅበራት የማጓጓዝ ችግር በማጋጠሙ አርሶ አደሮች ዩኒየኖች ላይ እንዲገዙ መደረጉን ገልጸዋል። ይህም በአርሶ አደሮች ላይ ያልተገባ መጨናነቅ እና መዘግየት እየፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታትም አካባቢያዊ አጓጓዦች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
እጥረት ባጋጠማቸው አካባቢዎች በወቅቱ ለማድረስ ወደብ ላይ የደረሰውን ማዳበሪያም የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በክልሉ የተሻለ ሥርጭት እንደሚኖር ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈለገውን ያህል ባይኾንም ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጋር በማቀናጀት ለመጠቀም የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በክልሉ አልፎ አልፎ ከሚታየው የሰላም ሁኔታ አኳያ ካልኾነ በስተቀር በዚህ ዓመት የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንደማያጋጥም ገልጸዋል። በሕገ ወጥ የማዳበሪያ ግብይት ላይ ተሳትፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ንብረቱን መወረስ ብቻ ሳይኾን በወንጀል የሚጠየቅ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
አርሶ አደሮችም ያገኙትን ግብዓት በግብርና ምክረ ሃሳብ መሠረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ ክልሉ ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተባዝቶ እየተዘጋጀ መኾኑን ነው ዶክተር ድረስ የነገሩን። ከዚህ ውስጥ ከ102 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ዘር ተዘጋጅቶ ወደ ዞኖች እየተሰራጨ መኾኑን አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
