”ስማርት (ዘመናዊ) ባሕር ዳርን እንጀምረዋለን፤ ትውልድ ይጨርሰዋል” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ

80

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባሕር ዳር ከተማን ”በስማርት (ዘመናዊ) ባሕር ዳር” ፕሮጀክት ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎች ሳቢ እና በዙሪያዋ ለሚገኘው ሕዝብም መልካም አርዓያ እንድትኾን ለማድረግ ሥራ ተጀምሯል። ”ስማርት ሲቲ” (ዘመናዊ ከተማ) የሚለውን ቅጽል በመጠቀም ስማርት (ዘመናዊ) ባሕር ዳር በሚል ተመሳሳይ መጠሪያ ለነዋሪዎቿ ምቹ፤ ለእንግዶቿ ተናፋቂ ባሕር ዳርን የማልማት እና የማዘመን ፕሮጀክት ተወጥኗል። ለዚህም ፕሮጀክት ተቀርጾ የጽሕፈት ቤቱ መቋቋም በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ከሰሞኑ ጸድቋል። ለ2016 በጀት ዓመትም 116 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ስለ ”የስማርት ባሕር ዳር ከተማ ፕሮጀክት” ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ አተገባበር እና ከባለ ድርሻ አካላት ስለሚጠበቀው ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ስማርት ሲቲ” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ለአገልግሎት አሠጣጥ፣ ለአመራር እና ለተገልጋይነት የሚዘረጋ ሥልጡን እና ምቹ መስተጋብር መኾኑን ነው ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የገለጹት። ”ቴክኖሎጂ በፈጠራቸው መገልገያዎች በመጠቀም አገልግሎትን በማፋጠን እና መስተጋብርን በማዘመን ህይወትን ቀላል ማድረግ ነው” ሲሉም ጠቅሰውታል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሙስና እና ሌሎች ችግሮችም አገልግሎትን በማዘመን ይቀነሳሉ ብለዋል።

የፌዴራል ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ባወጣው ስትራቴጂ መሠረት ስማርት ሲቲ (ዘመናዊ ከተማ) ለመፍጠር ስድስት መሠረታዊ ምሰሶዎችን መተግበር ወይም ማሟላት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አስሜ እነርሱም፦

👉 ስማርት ኢኮኖሚ (ሥልጡን የምጣኔ ሃብት መስተጋብር) – ንግድ፣ ልማት እና የመሳሰሉትን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ማሳለጥ፤
👉 ስማርት ሞቢሊቲ (ሰላማዊ እንቅስቃሴ) – ደኅንነቱ በካሜራ የሚጠበቅ አካባቢ እና ዘመናዊ መጓጓዣ፤
👉 ስማርት ኢንቫይሮመንት (ለኑሮ ተስማሚ ከባቢ) – ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የኾነ ህይወት መኖር (ለምሳሌ ለመንገድ መብራቶች ታዳሽ ኀይልን መጠቀም፣ የአረንጓዴ ልማት እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን፣ የውበት ሥራዎችን መቆጣጠር)፤
👉 ስማርት ላይቪንግ (ምቹ አኗኗር) – የመኖሪያ ቤቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለእይታ ያማሩ፣ ያሉበት የሚታወቅ፣ ለካሜራ እና ለመሠረተ ልማት የተመቹ፣ ወዘተ ማድረግ
👉 ስማርት ገቨርናንስ (የተሳለጠ አሥተዳደር) – እያንዳንዱ ተቋም አገልግሎት አሰጣጡን በኢ – ሰርቪስ የሚያደርግበት፣ ተገልጋይ ቤቱ ኾኖ በሲስተም የሚገለገልበትን አሠራር ማዘመን እና ማስፋፋት ነው። (ለምሳሌ የመሬት፣ የንግድ፣ የገቢ፣ የጤና ተቋማትን ወዘተ. የአሥተዳደር እና የአገልግሎት ሥርዓቱን በኢ-ገቨርናንስ (የበይነ መረብ ሥርዓት ማስተሳሰር እና ማዘመን)

👉 ስማርት ሪዝደንስ (ሥልጡን ነዋሪ (ዜጋ) – ከላይ የተጠቀሱትን አምስቱ የስማርት ከተማ (ዘመናዊ ከተማ) ምሰሶዎችን የሚያስተሳስር እና መጠቀም የሚያችል ማኅበረሰብ ማለት ነው። ለዚህም የስማርት ከተማ ጥቅምን በማስገንዘብ ከሞባይል እና ኤሌክትሮኒክስ ጋር የተዋወቀ ማኅበረሰብ መፍጠርን ይጠይቃል። ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል፣ አገልግሎቶቹን በእጁ እና በቤቱ ካሉ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር ዘመናዊ ሕዝብ እንዲኾን ማድረግ ነው። ተከባብሮ እና ተቻችሎ መኖር፣ የስማርት ሕዝብ መገለጫዎች ናቸው። አንዲት ከተማም ስማርት (ዘመናዊ) ልትኾን የምትችለው ሕዝቡ ስማርት (ዘመናዊ) ከኾነ ነው። ህይወትን ቀላል አድርጎ ለመኖር በሰላም፣ በመተሳሰብ እና በመቻቻል ሲኖር አንድ ሕዝብ ስማርት ነው ይባላል በማለት ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል።

”በከተማ አሥተዳደሩ ወሳኝ ጉዳዮችን ለይተናል፤ ከእነዚህም ውስጥ ቅድሚያ የተሰጠው ከተማችንን ማዘመን ነው” ያሉት ምክትል ከንቲባ አስሜ ለስማርት (ዘመናዊ) ባሕር ዳር መፈጠር የሚያግዙ መሠረተ ልማቶች መሠራታቸውን ጠቁመዋል። የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት በሙሉ፣ የንግድ ፈቃድ እድሳት እና የግብር አሠባሠብ ሥርዓቱ ደግሞ በከፊል በኮምፒዩተር ሥርዓት መግባቱ፣ ከወረቀት ንክኪ ነጻ የኾነ ህክምና መጀመሩን፣ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መጀመሩ፣ የውኃ ክፍያ በባንኮች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መጀመሩንም በአብነት ጠቅሰዋል። ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተገኙ 26 ካሜራዎችም ለዚሁ ዓላማ ይውላሉ፤ ተጨማሪ ሲስተሞችን የማልማቱ ሥራም ይቀጥላል ብለዋል።

ሥልጡንነት እና ዘመናዊነት ከግለሰቦች ጀምሮ ቀስ በቀስ የሚዳብር መኾኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባ አስሜ፦

👉 ማኅበረሰቡ ራሱን ለዘመናዊነት እንዲያዘጋጅና
👉 የንግድ ድርጅቶች የራሳቸውን የደኅንነት ጥበቃ ካሜራ ለመጠቀም እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

ምክትል ከንቲባው ይህንን ቃለ መጠይቅ ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ማቋቋሚያ ደንብ አጸድቋል። በ2016 በጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ 116 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም ምክትል ከንቲባው አሳውቀዋል።

ስልክ፣ ኢንተርኔት እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ዓለማቀፋዊ ትስስሩ አስገድደው ያስገቡን የለውጥ ምክንያቶች መኾናቸውን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባ አስሜ ”ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ መፈጠሩ ካልቀረ ተጠቅሞ ህይወትን ቀለል ማድረግ እንደሚሻል” መክረዋል።

ለሥራው ግብረ ኀይል ተቋቁሞ ተሞክሮ የተቀሰመ መኾኑን እና በቀጣይም የምቹ ሁኔታዎች ጥናት እንደሚደረግ ተጠቅሷል። በታየው ተሞክሮ መሠረት የትምህርት ተቋማት ትብብር ሥራውን ያቀለለ በመኾኑ ለስማርት(ዘመናዊ) ባሕር ዳር ከተማ ፕሮጀክት ስኬትም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጠንካራ የበጎ ፈቃድ ድጋፍ እንደሚፈለግ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቢጂአይ ኢትዮጵያ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የመማሪያ ክፍል ግንባታ ማስጀመሩን ገለጸ።
Next articleቀድመው ዘር በሚጀምሩ አካባቢዎች ማዳበሪያ የማስገባት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።