
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ችግሮችን በንግግር እና በይቅርታ መፍታት የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ኀላፊነት እና ሥራ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት፣ ሀገራዊ ፍቅር እና ግለሰባዊ ሥነ ምግባር የሚታነፁባቸው ተቋማት ባለቤት እንደኾነች ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም በሰላማዊ ውይይት እና እርቅ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። “ለመግባባት እና ለመነጋገር ድልድዮችን መፍጠር እንችላለን” ያሉት ዶክተር ከይረዲን በአንድነት የተሻለ ነገን መፍጠር ይቻላል ለዚህም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የደቡብ ኦሞ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በኢትዮጵያ የሃይማኖት አንድነት እና መከባበር የቆየ እና እረጅም ታሪክ ያለው እንደኾነ አስረድተዋል። “የእምነት ዕሴቶቻችንን ወደ ቀደመው በመመለስ ለሀገራችንም ኾነ ለዓለም መልካም ነገሮችን ልናበረክት ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የፌዴራል ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱላዚዝ አብዱልወሊ መሐመድ ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ኢትዮጵያ ማዘጋጀቷ በሃይማኖት መከባበር እና መደጋገፍ ለዓለም አርዓያ እንደምትኾን ማሳያ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው እና አብረው እንዲሠሩ መንገድ የሚከፍት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች በሰላም ላይ ያላቸው አቋም እና አስተምህሮ ተመሳሳይ በመኾኑ ይህንን ዕድል በመጠቀም ለአንድነት እና ለሰላም መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ሼህ አብዱላዚዝ። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ “እኛ ኢትዮጵያውያን ለዓለም ከምናስተምረው ብዙ እሴቶቻችን መካከል የሃይማኖት መከባበር እና መቻቻል አንዱ ነው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ መኾኑን የገለጹት ፓስተር ፃዲቁ የሃይማኖት እሴቶችን በመከተል ለሀገር አንድነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሃይማኖት ትልቁ ሥራው ተከታዩን ከሐጥያት፣ ከዘረኝነት፣ ከራስወዳድነት እና መልካም ካልኾኑ ሥራዎች ማውጣት በመኾኑ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
