“ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ፎረም በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄደ።

28

ደሴ: ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የባለሃብቶች እና አጋር አካላት ፎረም “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። በፎረሙ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱን ጨምሮ የደቡብ ወሎ ዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው በፎረሙ የተገኙ ባለሃብቶች እንደተናገሩት የውይይት ፎረሙ መዘጋጀቱ መልካም መኾኑን በማውሳት በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ብሎም የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይሠራል ብለዋል። ዞኑ ያለውን እምቅ ሃብት በመጠቀም እና የግል ባለሃብቱ ኢንቨስት እንዲያደርግ በመጋበዝ ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በዞኑ ውስጥ ላሉ ሥራአጥ ወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እንሠራለን ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ፋጡማ ይማም ተናግረዋል።

“የደቡብ ወሎ ዞን በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገ መኾኑን እና በግብርናውም ዘርፍ በሰብል እንዲሁም በጥራጥሬ ምርት የሚታወቅ መኾኑ እና ለደረቅ ወደብ ቅርብ በመኾኑ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል። እንደ ሀገር እየተካሄደ ያለውን “ኢትዮጵያ ታምርት” እንቅስቃሴ ዘርፉ የሚሰጠውን ምርታማነት ማሳደግን ጨምሮ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማምረት አልሚ አካላትን በመደገፍ የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ተናግረዋል።

በፎረሙ በዞኑ ውስጥ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በዝርዝር ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ሲኾን በዞኑ ያለውን እምቅ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እና በቀጣይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተነግሯል።

ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጄኔራል አበባው ታደሠ አሁናዊ የሰላም ሁኔታን በተመለከተ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያዩ፡፡
Next articleፈረስ ቤትን ለመቆጣጠር የመጣው የጽንፈኛ ኃይል መመታቱን የጎጃም ኮማንድፖስት አስታወቀ።