ጄኔራል አበባው ታደሠ አሁናዊ የሰላም ሁኔታን በተመለከተ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያዩ፡፡

46

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የሰሜን ሸዋ ዞን አሁናዊ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በወደፊት የሥራ አቅጣጫ ላይ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አሸባሪውን ሸኔ እና ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራውን ጽንፈኛ ኃይል አከርካሪውን በመስበር በሁለቱም ዞን አንጻራዊ ሰላም መስፈን መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

ጄኔራል አበባው ታደሰ በከሚሴ ከተማ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ከፍተኛ አመራሮች እና ከሁለቱም ዞኖች ከተውጣጡ የአሥተዳደር አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ጽንፈኛው ኃይል አዲስ አበባን ለማተራመስ ይመቸኛል ብሎ አለኝ ያለውን ኃይል በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ሰግስጎ እንደነበረ አስታውሰዋል።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በወሰደው ፈጣን እርምጃ በሁለቱም ዞኖች የነበሩ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ጽንፈኞችን እርምጃ በመውሰድ ሀገር የማተራመስ ቀቢፀ ተስፋቸውን በማምከን ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

አሁን ለብቻው ተነጥሎ በየቦታው ተደብቆ የሚገኙ የጽንፈኛ ኃይሉ አመራሮችን የመመንጠሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ እና የኮማንዶ እና አየር ወለድ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔራሰብ አሥተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞን የሀገሪቷን ሰላም በማናጋት የሕዝቦቿን በሰላም የመኖር ዋስትናን ለማሳጣት ቆርጠው የተነሱትን ሁለቱንም ጽንፈኛ ኃይሎች በተገቢው መንገድ በመምታት የጥፋት ተልዕኳቸውን ማምከን መቻሉን ገልጸዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ከኦፕሬሽናል ሥራው ጎን ለጎን የአካባቢውን የፀጥታ ኃይል የማጠናከር እና የማደራጀት ሥራዎችን መሥራቱን በማስታወስ አሁን በሁለቱም ዞኖች ለፀጥታው ኃይል ተግዳሮት የሚኾን ኃይል እንደሌለም አረጋግጠዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊውችም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ራሱ ሞቶ ዜጎችን የሚያኖር ሕዝባዊ ኃይል መኾኑን በማስታወስ እና በዞናቸው ለተገኘው ሰላም ሠራዊቱ ለከፈለው መስዋዕትነት እና ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የላቀ ክብር እንዳላቸው አብራርተዋል።

በመጨረሻም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአሥተዳደሩ ላስመዘገበው የተረጋጋ ሰላም እና ፀጥታ እውቅና በመስጠት ለሠራዊቱ አመራሮች ልዩ ሽልማት ከምስጋና ጋር ተበርክቷል፡፡

መረጃው የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል አድማ ብተና አባላት ሕዝባቸውን ለመካስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸው አስታወቁ።
Next article“ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ፎረም በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄደ።