የአማራ ክልል አድማ ብተና አባላት ሕዝባቸውን ለመካስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸው አስታወቁ።

29

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ማርቆስ እና በዙሪያው ባሉ ወረዳዎች ላይ የተሰማሩ የአድማ ብተና አባላት እንደተናገሩት በተደረገላቸው የሰላም ጥሪ መሠረት ተሃድሶ በመውሰድ የሕግ ማስከበሩን ግዳጅ ውጤታማ በኾነ መንገድ እየፈጸሙ ይገኛሉ።
አባላቱ እንዳሉት የክልሉን ሕዝብ ወደ ነበረበት ሰላም፣ ልማት እና መረጋገት ለማምጣት ጽንፈኛውን ለማስወገድ በሚደረገው ስምሪት እስከ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው አድማ ብተና ሻምበል አዛዥ ተወካይ ዋና ሳጅን ያሬድ ገብረህይዎት ከዚህ በፊት ሕዝባችንን የበደልነውን ለመካስ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን በምስራቅ ጎጃም ዞን ሊባኖስ፣ ባሶ ሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ፣ በስናን ወረዳ ደብረ ዘይት በመሰማራት ጽንፈኛውን ቀጥተነዋል ብለዋል።

በቀጣናው ካለው ሠራዊት በሚደረግልን ሁለንተናዊ ድጋፍ ታግዘን በርከታ ድሎችን አስመዝግበናል። በቀጣይም በጥምረት በመሥራት ጽንፈኛው ቡድን ለሀገር ሰላም ስጋት ወደማይኾንበት ደረጃ እንዲደርስ ጠንክረን እንሠራለን ብለዋል።

የአድማ ብታና መቶ መሪ ረዳት ሳጅን ሰለሞን ጎበዜ እና ረዳት ሳጅን ሄለን ሰጠኽኝ በሰጡት አስተያየት ክልላችን ከገባበት የሰላም እጦት እንዲወጣ እና ጽንፈኛ ቡድኑ በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመቀልበስ አየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ጥያቄ የሚመለሰው በነፍጥ ሳይኾን በመነጋገር እና በመወያየት መኾኑንም አውስተዋል፡፡ በመደነጋገር ወደ ጽንፈኛው ቡድን የተቀለቀሉ ወጣቶች የመንግሥትን ጥሪ አክብረው በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እና ከሕዝባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በድል ለመወጣት እና የሀገራችን ሰላም ለመጠበቅ ከመከላከያ ጎን ተሰልፈን ግዳጅ ለመወጣት ቁርጠኞች ነን ብለዋል። በአሁኑ ሰዓት የጽንፈኛውን ቡድን ዓላማ ለማምከን የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኙ እና የስምሪት ሥራዎችን በውጤት ለመደምደም ጠንክረው እየሠሩ
መኾናቸውንም ተናግረዋል።

መረጃዉ፡- የጎጃም ኮማንድፖስት ነዉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን 12 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleጄኔራል አበባው ታደሠ አሁናዊ የሰላም ሁኔታን በተመለከተ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያዩ፡፡