የወልድያ ከተማን ጨምሮ የአጎራባች ወረዳዎችን ተስፋ ከፍ ያደረገው የጤና ተቋም ግንባታ!

23

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልድያ ከተማ ጤና መምሪያ ኀላፊ ዘላለም ጌታቸው ከተማ አሥተዳደሩ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ አምስት የጤና ጣቢያዎች ቢያስፈልጉትም ማኅበረሰቡ በሁለት ጤና ጣቢያ ብቻ እየተገለገለ አንዳለ ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ተገልጋዩ ማኅረሰብ ተገቢ አገልግሎት እና እርካታን እንዳያገኝ ምክንያት ይኾናል ነው ያሉት።

በራስ ዓሊ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ ከክፍለ ከተማው ባሻገር አጎራባች የጉባላፍቶ እና የራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪን ጨምሮ 40 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የጤና ጣቢያ ግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። ለግንባታው ማስጀመሪያ 20 ሚሊዮን ብር ከከተማ አሥተዳደሩ በዚህ ዓመት በጀት መያዙን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከተማ አሥተዳደሩ 13 ሺህ 900 ካሬ መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረግ ለግንባታ ማስረከቡን ነው ያስረዱት። የከተማውን ገቢ በማሳደግ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለማርካት ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም መገንባቱ የወላድ እናቶችን አንግልት ይቀንሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በወልድያ ከተማ የራስ ዓሊ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ እንደማኅበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም ዕትሟ
Next articleየማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪ ሀገራዊ ዕድሎች እና ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው።