በ18 ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት?

83

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በ2003 ዓ.ም ግንባታ ሲጀመር በሦስት ዙር ግዙፍ ፋብሪካ ለመገንባት ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጅ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዘግይቶም ቢኾን ወደ ግንባት መግባት የቻለው የመጀመሪያው ዙር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ እንኳን ወደ ማምረት መግባት አልቻለም።

ፕሮጀክቱ በወቅቱ 235 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት ሲኾን በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ይገባል ተብሎ ነበር ወደ ግንባታ ሥራ የተገባው። አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 75 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚይዝ ሲኾን 50 ሺህ ሄክታሩ በአማራ ክልል፣ 25 ሺህ ሄክታሩ መሬት ደግሞ በቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኝ ኩታ ገጠም ልማት ነው።

ፕሮጀክቱን ይገነባ የነበረው የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ፋብሪካውን በተቀመጠለት የጊዜ መርሐ ግብር ማጠናቀቅ አልቻለም። በዚህም መንግሥት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን ለቻይናው “ካምስ” ኩባንያ በመሥጠት ቀሪ ግንባታውን እንዲያከናውን አድርጓል።

ተቋራጩ በስምንት ወራት ውስጥ በከፊል ምርት እንዲያስጀምር፣ በ14 ወራት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አጠናቅቆ እንዲያስረክብ ነበር ውል የተሰጠው፡፡ መጋቢት 2011 ዓ.ም ውል ተወስዶ ወደ ሥራ ይገባል ቢባልም መንግሥት ውል ለወሰደው ኩባንያ መክፈል የሚገባውን 30 በመቶ ወጪ ሊከፍል ባለመቻሉ እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም ሥራው ሳይጀመር ቆይቷል። ፋብሪካው በወቅቱ ወደ ምርት ባለመግባቱ በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ስኳር አገዳ በማርጀቱ በአብዛኛው ከጥቅም ውጭ ኾኗል።

ግዙፍ ፕሮጀክት የካቲት 29/2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ደረጃውን የጠበቀ ስኳር የማምረት ሙከራ መጀመሩን ይፋ ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች አሁንም ድረስ እያመረተ አለመኾኑን ነው የፋብሪካው ሠራተኞች የነገሩን። የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እንዳሉት አሁን ላይ በፋብሪካው 1 ሺህ 500 ቋሚ እና ከ2 ሺህ በላይ ጊዜያዊ ሰራተኞች ይገኛሉ። ፋብሪካውን ጥር 2016 ዓ.ም ሥራ ለማስጀመር ቢታቀድም የመብራት ኃይል እጥረት በአካባቢው ከገጠመው የጸጥታው ችግር ጋር ተደማምሮ ወደ ማምረት ለማስገባት እንቅፋት ኾኗል። አሁን ላይ ሠራተኛው በአገዳ ልማት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እና መሥኖ ልማት ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፋብሪካው ለረጅም ጊዜ ወደ ማምረት ባለመግባቱ በልማቱ ተነሽ የኾኑ ኀላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች “መሬቱን መልሼ አገኛለሁ” በሚል እሳቤ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት አገዳ ልማት ላይ ጉዳት ስለማድረሳቸውም ከሠራተኞች መረጃ አግኝተናል። ችግሮች ተቀርፈውለት ፋብሪካው ወደማምረት የማይገባ ከኾነ የሚለማው አገዳ ስለሚያረጅ ከጥቅም ውጭ ሊኾን እንደሚችል ገልጸዋል። እንዲህ አይነት ኪሳራዎች ሲደማመሩ ቀጣይም የፋብሪካው ህልውና ሊፈትኑ እንደሚችሉ ሠራተኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱን ለመታደግ ኮንትራክተሮች ቀሪ ሥራዎችን ጨርሰው ፋብሪካውን ምርት እንዲያስጀምሩ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አገዳ ማልማት መቻሉን ያነሱት የመረጃ ምንጫችን ፋብሪካው በወቅቱ ወደ ማምረት ባለመግባቱ የታሰበውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም። በዚህ ዓመትም ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ፋብሪካው ወደ ሥራ ካልገባ ባለፋት ዓመታት እንዳጋጠመው የአገዳ ምርቱ ከጥቅም ውጭ ከመኾኑ ባለፈ በቀጣይ ዓመት ሌላ ምርት ለማዘጋጀት ችግር ይፈጥራል።

ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ቢገባ በቀን 12 ሺህ ኩንታል አገዳ የመፍጨት አቅም አለው። ፋብሪካው ቶሎ ወደ ማምረት እንዲገባ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል ሠራተኞች። ፕሮጀክቱ ያሉበትን ችግሮች እና በቀጣይ የተቀመጡለትን የትኩረት አቅጣጫዎች ምን እንደኾነ የፕሮጀክቱን ኀላፊ ሃሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። መረጃውን ፈቃደኛ ኾነው እንደሰጡን ለተከታታዮቻችን የምናደርስ ይኾናል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከባሕላዊ አሠራር መውጣት ይጠበቅብናል” አቶ ኃይሉ ግርማይ
Next articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም ዕትሟ