“የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከባሕላዊ አሠራር መውጣት ይጠበቅብናል” አቶ ኃይሉ ግርማይ

18

ሰቆጣ: ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ የእናቶች፣ ሕጻናት እና የአፍላ ወጣቶች ጤና እና ሥርዓተ ጾታ ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩም የብሔረሰቡ ዋና አሥተዳዳሪን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና የሥርዓተ ጾታ ክበብ አባል ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ዋና አሥተዳዳሪው ኃይሉ ግርማይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከባሕላዊ አሠራር ለመውጣት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በርካታ አካባቢዎች ከጤና አገልግሎት ውጭ ኾነው በመቆየታቸው እናቶች በባሕላዊ መንገድ እንዲወልዱ እንደተገደዱ አቶ ኃይሉ ገልጸዋል። ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ ሰላማችንን መጠበቅ ይገባናል ብለዋል።

ያለውን ሰላም ተከትሎ በአሥተዳደሩ ሁሉም አካባቢዎች የጤና ተቋማትን በመክፈት የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ እየሠራን ነው ብለዋል።

የብሔረሰቡ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ አሰፋ ነጋሽ በሰላም ማጣት ምክንያት በዘጠኝ ወሩ ብቻ በወሊድ 20 እናቶች እና 74 ጨቅላ ሕጻናት እንደሞቱ ገልጸዋል።

ሰላማችንን በማስጠበቅ፣ የጤና ተቋማትን በመክፈት የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ሞት መቀነስ እንችላለን ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊ የጻግቭጂ ወረዳ ጤና ባለሙያ ወይዘሮ ታምር አቡሽ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከእናቶች ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሌላው ተሳታፊ አቶ አበራው ማሞ የእናቶችን ጤና መጠበቅ ተተኪ ትውልድን ማዳን እንደሆነ ጠቁመዋል።

ተሳታፊዎች የደም ልገሳ ካከናወኑ በኃላ ውይይቱ ተጠናቅቋል።

ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ በጸጥታ ችግር ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ወጣቶች ገለጹ።
Next articleበ18 ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት?