
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ሥር ውለው በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት የቆዩ 1 መቶ 38 ወጣቶች ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ወጣት ዘላለም ጸሐይ በቁጥጥር ሥር ከዋለ ጊዜ ጀምሮ ስለሰላም መሠልጠኑን ተናግሯል፤ ለሁሉም ሊሰጥ የሚገባ ሥልጠና ወስደናል ነው ያለው። ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በውይይት መፍታት እንደሚገባ እና የሰላምን አስፈላጊነት እንደሚያስተምር ተናግሯል።
ወጣት ኬኔዲ ካሳሁን በበኩሉ ስለሰላም ትምህርት መሰጠቱን ገልጿል፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ስለመፍታት መማሩንም ተናግሯል። ለግጭት መንስኤ የሚኾኑ ነገሮችን መፍታት እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስም ለሰላም እንደሚጠቅም መረዳቱንም ጠቅሷል።
ሰላም ሲኖር ሠርቶ መብላት እና ፍላጎትን ማሳካት እንደሚቻል የገለጹት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ተሻገር ባዬ ናቸው። ታራሚዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲመለሱ ለሰላም አጥብቀው እንዲሠሩ አሳስበዋል። ወጣቶች የሌላ አካል ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንዳይኾኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት ማስተማሪያ እንጂ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንደሚያራግቡት የስቃይ ቦታ አለመኾኑን ታራሚዎቻችን ምስክር ናቸው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!