
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመማር ማስተማሩን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በምግብ ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች እንዳይኖሩ እና ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ለማድረግ በየትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር ይካሄዳል፡፡
አሁን አሁን በኢትዮጵያ የተማሪዎች የምገባ ሥርዓትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ በአማራ ክልል በየትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር እውን እየኾነ መጥቷል፡፡ ይሄም ተማሪዎችን ለትምህርት ፍቅር እንዲኖራቸው እና ትኩረት እንዲያደርጉ እያደረጋቸው መኾኑ ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የተማሪዎችን ምገባ ፕሮግራም ማስኬድ ለትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማነት አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ ሙሉ ጊዜያቸውን ንቁ ኾነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ በተማሪዎች ውጤት ላይ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የተማሪዎች ምገባ ሥርዓት እየተካሄደ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ የክልሉ መንግሥት 75 ሚሊዮን ብር በመመደብ በድርቅ በተጎዱ ወረዳዎች የምገባ ሥርዓት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በድርቅ በተጎዱ ወረዳዎች ምገባው የተካሄደው በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞን መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
የምገባ ሥርዓቱን ሰፋ አድርጎ ለመስጠት ሰፋ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ከተማ አሥተዳደሮች ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምገባ ማካሄድ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምገባ ላይ ያለው አመለካከት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በ454 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መኾኑን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ 224 ሺህ 563 ተማሪዎች እንደሚመገቡም አስታውቀዋል፡፡ ምገባው በዋናነት እየተካሄደ የሚገኘው በመንግሥት እና በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አማካኝት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በስፋት እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው የምገባ ሥርዓት በቂ አይደለም ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ የምገባ ሥርዓቱን መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡ ምገባ ተቋማዊ በኾነ መንገድ እንዲመራ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎች ምገባ ለትምህርት ጥራቱ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ በኩል ታላቅ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምገባ ሲጀመር አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ ምገባ ያለባቸው ትምህርት ቤቶች ምገባ ከሌለባቸው ትምህርት ቤቶች የበለጠ ተማሪዎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል፡፡ ምገባ ከሌለባቸው ትምህርት ቤቶች ምገባ ወደ አለባቸው ትምህርት ቤቶች ለመሄድ የሚጠይቁ ተማሪዎች ቁጥር በርካታ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ምገባን ማስፋፋት እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ከተሞችን ጨምሮ ድርቅ በተከሰተባቸውም ኾነ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች ምገባ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ የምገባ ጉዳይ ለአንድ አካባቢ ብቻ ሳይኾን በሁሉም አካባቢዎች መጀመር ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ምገባ ያደጉ ሀገራት ጭምር የሚተገብሩት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የምገባ ሥርዓት በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ አስተዋጽኦው የጎላ መኾኑን በመገንዘብ ለተፈጻሚነቱ ርብርብ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!