ከአዙሪት ያልተላቀቀው ህልም

102

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምንኖረው በአብዛኛው ለእለት ጉርሱ ያገኛትን ሠርቶ በሚበላ እና ለፍቶ አዳሪ በሚባል ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ነገር ግን ይኽ ማኅበረሰብ የነገን አርቆ በማሰብ ጥሪት ይቋጥራል። የነገውን ህይዎት ለማሳመርም ይጥራል ይግራል።

ለፍቶ አዳሪው ሩቅ አሳቢ ነው እና ከሚያገኛት ቆጥቦ ለነገው ተስፋ ማሳኪያ ባለው አቅም ሁሉ ባገኘው የገንዘብ ማጠራቀሚያ መንገድ ሁሉ ያስቀምጣል።

እኔ ያለሁበት ቀየ ላይ የአንድን የቅርብ ሰው ታሪክ ለዛሬው ትዝብቴ እንደመነሻ አድርጌ ላጋራችሁ ወድጃለሁ።

ግለሰቡ ለፍቶ የሚያድር ሩቅ አሳቢ እና ራሱንም ሀገርንም ሊጠቅም የሚችል ሥራ መሥራት እንደሚፈልግ ከሚያነሳው ሃሳብ መረዳት ይቻላል።
ይህንን ተግባሩንም ለመወጣት ያስችለው ዘንድ በወር ከሚያገኛት ገቢው ላይ ይቆጥባል። ነገን እውን ለማድረግም ብቸኛው አማራጭ ይሄ እንደኾነ በተደጋጋሚም ሲያወራ እሰማዋለው።

አንድ ቀን ታዲያ ከዚህ ወዳጀ ጋር ሞቅ ያለ የደራ ወሬ ይዘን ስንጨዋወት ለመኾኑ ሃሳብህ የት ደረሰ? ለምን የሚያበድርህ ሰው ፈልገህ ህልምህን አታሳካም? ስል እንደቀልድ ሃሳብ አነሳሁ።

ልጁ ትንሽ እንደመተከዝ ብሎ ባክህ ጉዱ ብዙ ነው ሲል ሃሳቡን በአጭር አስተያየት ሊቋጭ ፈለገ። እኔም የምን ጉድ ነው ስል ሃሳቡን ዘርዘር አድርጎ እንዲያስረዳኝ በመፈለግ ጎተጎትኩት።

እሱም እየውልህ ዛሬ ጊዜ ብድር እኮ እንደፈለከው የሚያበድርህ አታገኝም አለኝ። እኔም አሽ ሃሳብህን ለማሳካት የምትቆጥበው ገንዘብስ አያግዝህም? አልኩ ጥያቄ ባዘለ ድምፀት።

እሱም አይ አንተ እሱም እኮ በየጊዜው በዓል በመጣ ቁጥር አየተነሳለት ምን ቀረው ብለህ ነው አለኝ።

እኔም ምን ለማለት ፈልጎ እንደኾነ ጠየቅኩት። እሱም “ከጉረቤት አታሳንሰኝ” በሚል የወላጆቹ ጥያቄ ያለች የሌለች ጥሪቱን ለበዓል መዋያ ለቤተሰቡ እንደሚያውለው አስረዳኝ።

እንዴት እንዲህ ሊኾን ይችላል? ሰው እኮ “እንደ ቤቱ እንጅ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም” ደግሞ ስትለፋበት የከረምከውን ጥሪት በበዓል ምክንያት ማባከኑስ ጥሩ ነው ስል ሳይታወቀኝ ምክር ቢጤ ወርወር አደረኩ።

ያልተያዘ ግልግል ያውቃል የሚል ተረቱን ከተረተ በኋላ የተጣባን ባሕል እንዲህ በቀላል ይለቀናል ብለህ ነው አለኝ። እኔም በመስማማት ሃሳብ አንገቴን ነቀነቅኩ።

እሱም ቀጠል አድርጎ ወላጆቸ ከጉረቤቶቻቸው በዓልን አንሰው ሊውሉ መኾኑን ሳስብ የሩቅ ህልሜ ጨርሶ ይጠፋል።

ሃሳቤ እነሱን ማስደሰት ብቻ ይኾናል። ደግሞም ያደኩበት ባሕል ጥቃት አይወድም፤ ሌሎች ወላጆቻቸውን ሲያስደስቱ እኔስ የሚለው ወኔ አቅል አስቶ ያለችውን ጥሪት ለበዓል መዋያ አደርጋትና እንደገና ቁጠባው ይጀምራል ሲል አዙሪቱም ተስፋውም ዓመታት ቢነጉዱም አሁንም በተስፋ እንዳሉ ነገረኝ።

ይህን ትዝብቴን በቅርብ ጓደኛየ ለማንሳት ሞከርኩ እንጅ የአብዛኞችን ቤት ያንኳኳ ብዙዎችን ለችግር የጣለ ጉዳይ ነው።

ዓመት በዓል ሲመጣ ሁሉም ያለችውን አራግፎ ተደስቶ ለመዋል ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል።

ይህ ሂደት ደግሞ ሁሉም እንደራሱ ቤት ሳይኾን በፉክክር ከጎረቤት ጋር የሚካሄድ በመኾኑ አላስፈላጊ ወጭዎች ሲወጡ የሚስተዋልበትም ነው።

በዚህም የተነሳ የብዙዎች ቤት ከአዙሪት ያልተላቀቀ ፈተና ገጥሞት ተረብሿል። ሀገርን ማቃናት የሚችሉ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዳይኾኑ በማድረግ ህልምን አጨናግፏል። የበዓል ወጭን በሚመለከት ከአንድ ቀን ደስታ እና ፌሽታ በላይ ቆም ብሎ አሰቦ በመጠኑ እንደራስ ማድረግም፤ ማደግም ያስፈልጋል።

“ሰው እንደ እራሱ እንጅ እንደ ጉረቤቱ አይኖርም” የሚል ብሂል ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ኾነን ሳለ ራሳችንን ኾነን መኖር እና ማለፍ ለምን ተሳነን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳምንቱ በታሪክ
Next article“ከ224 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እየመገብኩ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ