
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቅዱስ ያሬድ ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ ቀለም አልዘልቅህ አለው፤ ከመምህሩ ጠፍቶ ሲጓዝ ከአንዲት ዛፍ ስር አረፈ፡፡ አንዲት ትል ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ ወዳቃ በሰባትኛው ሲሳካላት ተመለከተ፡፡
የትሏን ተስፋ አለመቁረጥ የተመለከተው ብላቴና ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቃርታ ጠይቆ ትምህርቱን እንደቀጠለ በተለያዩ ድርሳናት ተከትቦ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አስተዋጽኦ እና ስፍራ ያለው ቅዱስ ያሬድ ከአባቱ ከይስሐቅ ከእናቱ ክርስቲና ተወልዶ ገና በሕጻንነቱ ወላጆቹ በልጅነቱ ስለሞቱበት ከአጎቱ ጋር ኾኖ እድሜውን በትምህርት አሳልፏል፡፡ በሂደትም በርካታ መንፈሳዊ መገለጦች እንደተፈጸመለት እና ሃይማኖታዊ አበርክቶው ከፍተኛ እንደኾነ ሃይማኖዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
በቤተክርስቲያኗ ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ በመባል የሚታወቁትን የዜማ ዓይነቶች የደረሰው ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በያዝነው ሳምንት ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም በአክሱም ነበር፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ መገልገያ ኾነ፡፡ በቅዱስ ያሬድ የተደረሱት የዜማ መጻሕፍት ድጓ፣ ጾመድጓ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት እና ምዕራፍ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ይዘት ባላቸው ድርሰቶቹ የሚታዩት የቃላት አጠቃቀም፣ የሚስጥር፣ የዘይቤ አገላለጥ እና መሰል ጥበቦች ቅዱስ ያሬድ ከፍተኛ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥኦ እንደነበረው ለመረዳት ይቻላል፡፡
—/////—–//////——///////——/////
የአጼ ቴዎድሮስ ሕልፈተ ሕይወት
የግዛት አንድነቷን በማስጠበቅ፣ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት እና ሥልጣኔን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት እና መሠረት የጣሉት አጼ ቴዎድሮስ ይህ የአዲስ ትውልድ ጅማሬያቸው ከዘመኑ ቀድመው የተወለዱ አስብሏቸዋል፡፡
ለሥልጣኔ ባላቸው ከፍተኛ ጉጉት ከአውሮፓውያን ጋር ለመወዳጀት ጥረት ቢያደርጉም ሚሲዮናውያን እና ጉዳይ ፈጻሚዎች በሚያደርጉት ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እና ንቀት እየበሸቁ ለተደጋጋሚ ግጭት መዳረጋቸውም ይታወቃል፡፡ ያልተረጋጋው የአውሮፓውያን ግንኙነታቸው ከእንግሊዝ ጋር የበለጠ አጋጫቸው፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት የጠየቁትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አለማቅረቡ እና የአውሮፓ ሚሲዮናውያን ስለላ እና ጣልቃ ገብነት ያስቸገራቸው አጼ ቴዎድሮስ የእንግሊዝን ጨምሮ የጀርመን እና የፈረንሳይ ሚሲዮናውያን እና ጉዳይ ፈጻሚዎችን በንዴት አሰሯቸው፡፡
ጉዳዩን በጥንቃቄ እና በዲፕሎማሲያዊ ልስላሴ ለመፍታት ሞክረው ያልቻሉት እንግሊዞች በነሐሴ 1859 ዓ.ም ዜጎቻቸውን ለማስፈታት በጄኔራል ናፒየር የሚመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላኩ፡፡ በቴዎድሮስ ላይ ባኮረፉ መሳፍንት እና መኳንንት እየታገዘ ከምጽዋ ወደ መቅደላ የተጓዘው የእንግሊዝ ጦር ሚያዝያ 2 ቀን 1860 ዓ.ም በመቅደላ ጥግ ባለችው እሮጌ ላይ በፊታውራሪ ገብርየ ከሚመራው የአጼ ቴዎድሮስ ጦር ጋር ገጥሞ ፊታውራሪ ገብርየ ተሰው፡፡
ከቀናት በኋላም የእንግሊዝ ጦር አጼ ቴዎድሮስ በመሸጉበት በመቅደላ አንባ ላይ የተጠናከረ ጥቃት ከፈተ፡፡ ድሉም የእንግሊዞች ኾኖ ወታደሮች ቴዎድሮስን ለመማረክ በተቃረቡ ጊዜ አጼ ቴዎድሮስም በዙሪያቸው የሚገኙ ወታደሮቻቸውን እንዲሸሹ አሰናብተው እርሳቸው ግን በእንግሊዝ ጦር ላለመማረክ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ፡፡ ይህም ቀን በያዝነው ሳምንት ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ነበር፡፡
—/////——///////——/////—–////
የቃኘው ሻለቃ ዘማች ጦር ወደ ኮሪያ መጓዝ
በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በተፈጠረው ጦርነት ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት እንድትሳተፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀረበላት ጥያቄ መሠረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከግንቦት 1950 እስከ ሐምሌ 1953 በተካሄደው ጦርነት ላይ በአጠቃላይ 6 ሺህ 37 ሠራዊት አዝምታለች፡፡
ከአፍሪካ የዘመተው ብቸኛው እና ቃኘው ሻለቃ የሚል ስያሜ የተሰጠው ኢትዮጵያዊ ዘማች ጦር በኮሪያ ልሳነ ምድር በጦርነት በቆየበት ጊዜ ጀግንነትቱን እና ሞት አይፈሬነቱ አሳይቷል፡፡ ከአሜሪካ ጎን ኾነው ከዘመቱ 21 ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙዩኒስቶች እጅ የወደቁ ዘማቾች ሲኖራቸው ከኢትዮጵያ ግን 122ቱ በጦርነቱ ሞተዋል፤ 536 ወታደሮች ቆስለዋል እንጂ አንድም የተማረከ የለም።
በድፍረት፣ በጀግንነት፣ በስልት እና ለቆሙለት ዓላማ እስከ መስዋዕትነት በጽናት መቆምን ለዓለም ያሳየው ኮሪያ ዘማች ኢትዮጵያዊ ጦር ቃኘው ሻለቃ የመጀመሪያ ዙር 1 ሺህ 122 ዘማቾች ለዘመቻ ከኢትዮጵያ የተንቀሳቀሱት ሚያዚያ 5 ቀን 1943 ዓ.ም ነበር፡፡
ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሰጡት መመሪያ “ይሄን ሰንደቅ ዓላማ መመሪያ አድርጋችሁ እንድትዘምቱ፣ በተሰማራችሁበት ቦታ ጀግንነት ሠርታችሁ በደረታችሁ ላይ ልዩ ምልክት አድርጋችሁ በኩራት ስትመለሱ በአደራ የሰጠናችሁን ዓርማ መልሳችሁ እንድታስረክቡን” እንዳሉ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ምንጮቻችን፦
-አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ሚያዝያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም
-ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ የቅዱስ ያሬድ ታሪክ እና የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ፤ 1999 ፤
– ጳውሎስ ኞኞ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት፤ የኢትዮጵያ ታሪክ 2001
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!