
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ምርት ውል በኢትዮጵያ ከ70 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ አሠራር ቢኾንም አሠራሩ በሕግ የተደገፈ ባለመኾኑ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጥቅም ማግኘት ሳይቻል ቆይቷል።
አሠራሩን በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን በሀገር አቀፍ ደረጃ የአምራች እና አስመራች ግንኙነትን የሚወስን አዋጅ ቁጥር 1289/2015 እንዲወጣ ተደርጓል። አዋጁ ከሰኔ 29/2015 ጀምሮ የጸደቀ ሲኾን በሁሉም ክልሎች አዋጁን የማስገንዘብ ሥራ አየተሠራ መኾኑን በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ ገልጸውልናል።
የግብርና ምርት ውል የተለያዩ አግባብነት ያላቸው ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚፈልግ መኾኑ፣ የአምራች እና አስመራች ግንኙነት እንዲፋጠን የሚደግፉ የሦስተኛ ወገን አካላትን ተሳትፎ ስለሚፈልግ እና በአምራች እና አስመራች መካከል ያለውን የመደራደር ልዩነት ለመቀነስ እንዲቻል አዋጁ እንዲወጣ ተደርጓል ብለዋል።
አዋጁ ታላላቅ ተሞክሮዎች፣ ቴክኖሎጅዎች እና ካፒታል ያላቸው ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ከአርሶ አደሮች ጋር ውል ገብተው በአርሶ አደሮች ማሳ በማምረት ምርት ማግኘት እንዲችሉ የማድረግ አቅም እንዳለው ነው የተገለጸው። ይህም አምራች እና አስመራቹ በምጣኔ እና በቴክኖሎጅ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያደርጋል ብለዋል። አዋጁ የእያንዳንዱን ባለ ድርሻ አካላት ሚና ለይቶ ያስቀመጠ በመኾኑ በተቀናጀ መንገድ ሥራውን መሥራት ያስችላል ተብሏል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አጀበ ስንሻው ክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአሠራር መመሪያ (ጋይድ ላይን) በማዘጋጀት የግብርና ውል እርሻ ሲተገብር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ፤ ምርታማነት እንዲያሳድጉ እና አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን ምርትም በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ፣ ብድር እንዲያገኙ እና ኢንዱስትሪዎችም ግብዓት እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።
በ2013/14 የምርት ዘመን ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በግብርና ውል በማረስ ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።
ይሁን እንጅ የጠራ እና አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ የተቋማት ቅንጅት ችግር፣ አስመራቾች አቅም ሳይኖራቸው ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባት እና የደላላ ጣልቃ ገብነት አሠራሩን ሲፈትኑት መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣው አዋጅ ችግሮችን የሚፈታ እና የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ይበልጥ የሚያጎለብት መኾኑን አንስተዋል።
የጃዊ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበራ ባዘዘው እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የውል እርሻ የሕግ ማዕቀፍ መውጣቱ ትርፍ አምራች በኾኑ አካባቢዎች የሚገኙ አምራቾችን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል።
በተለይም ደግሞ አምራቾች የግብርና ግብዓት ከአስመራቹ በወቅቱ እንዲያገኙ እና ያመረቱትን ምርት በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ እንደሚያደርግም አንስተዋል። አስመራቹ እና አምራቹ ሳይተዋወቁ በደላላ ያደርጉት የነበረውን ሥምምነት እንደሚፈታም ገልጸዋል። በዚህ ዓመት የተሟላ ግብዓት የማያቀርብ አስመራች በወረዳው ተቀባይነት እንማይኖረው ገልጸዋል።
በምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የግብዓት ቡድን መሪ ሞላ ፈረደ እንዳሉት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ራሱን የቻለ የውል እርሻ አዋጅ ባለመዘጋጀቱ አስመራቹ ውል በያዘው መሠረት ምርት ያለመግዛት፣ አምራቹም የተሻለ ገበያ ሲያገኝ ውል ከወሰደው አስመራች ውጭ የመሸጥ ችግሮች ነበሩ። አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሕግ መውጣቱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን ያሻሽላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በዚህ ዓመት በወረዳው ውል ከወሰዱ 100 አስመራቾች ውስጥ 53ቱ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!