የዓለም የሥነ ጥበብ ቀን እና የኢትዮጵያ ጃዝ ቀን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መከበር ጀመረ።

42

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥዕል እና የጃዝ ሥራዎች የሚቀርቡበት ዝግጅቱ ለአንድ ሳምንት ለሕዝብ ክፍት ኾኖ ይቆያል።

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል እና አለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይንት ትምህርት ቤት በጋራ በዓለም ለስድስተኛ ጊዜ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የሥነ ጥበብ ቀን እና የኢትዮያ ጃዝ ቀን እንዲከበር አድርገዋል።

ዝግጅቱ የአካዳሚው ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሀንስ፣ ሠዓሊ እና ቀራጺ በቀለ መኮንን፣ የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበባት እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሠርፀ ፍሬስብሃት በተገኙበት ተከፍቷል።
ቀደምት እና በአለ የሥዕል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ተማሪዎች የተሠሩ ባሕልን እና ጥበብን አዋደው ለትውልድ የሚያሻግሩ ሥራዎች በኤግዚቢሽኑ ቀርበዋል ያሉት ሠዓሊ እና ቀራጺ በቀለ መኮንን ናቸው።

አቶ ሠርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው ይህንን ታላቅ ቀን ስናከብር ለሥነ ጥበባት እና ጃዝ ትልቅ ቦታ መስጠት ለትውልዱ እንደሚያስፈልገው በማሰብ እና ታላላቆችን ማስታወስ አስፈላጊ በመኾኑ ነው ብለዋል። ለታዳጊዎችም ጥበብን ማውረስ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የጃዝ አባት የኹኑትን ሙላቱ አስታጥቄን ፈለግ የተከተለው ሳሙኤል ይርጋ የጃዝ ሙዚቃውን እንደሚያቀርብም ተገልጿል።
የሊዮናርዶ ዳቬንቺ የልደት ቀንን የዓለም የሥነ ጥበብ ቀን በማድረግ እንዲከበር ያደረገው ዩኔስኮ ነው።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሜጋቢት 30/2016 ም.አ ቺርቤዋ ጋዚቲ
Next articleለለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ የሚያገለግሉ ከባድ ማሽነሪዎች ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ቤት እየተጫኑ ነው።