የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የኦሎምፒክ ችቦን ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አስረከበ።

36

ደሴ: ሚያዝያ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በደሴ ከተማ ያዘጋጀው የኦሎምፒክ ችቦ ርክክብ በተለያዩ አዝናኝ እና ስፖርታዊ ዝግጅቶች ታጅቦ ተካሂዷል።

በደሴ ከተማ በተካሄደው የኦሎምፒክ ችቦ ርክክብ ሥነሥርዓት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ፣ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው ሥራ አሥፈፃሚዎች፣ የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ቢልልኝ መቆያ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥራ አሥፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ይህን እድል በማግኘቷ መደሰታቸውን እና ከሰላም ወዳዱ የከተማዋ ነዋሪ እና ከሥራ ኀላፊዎች ጋር በመቀናጀት የተሳካ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ስፖርት የዓለምን ሕዝብ ያለልዩነት በአንድ ጥላ ስር የሚያሠባሥብ ታላቅ ማኅበራዊ ሁነት መኾኑን በመጥቀስ በሕዝቦች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር፣ የሰላም፣ የልማት፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት ስሜት ማንፀባረቂያ በመኾኑ ከኦሮሚያ ክልል የተረከብነውን ችቦ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስረክበናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ዳዊት አስፋው የደሴ ከተማ ላዘጋጀው ደማቅ ሥነሥርዓት በኦሎምፒክ ኮሚቴው ስም ምሥጋና አቅርበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባሕል ቱሪዝም ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ ፋንታሁን ብላቴ የኦሎምፒክ ችቦን ለመቀበል ወደ አማራ ክልል ደሴ ከተማ በመምጣታቸው መደሰታቸውን እና ለተደረገላቸው አቀባበል አመሥግነዋል፡፡ በደማቅ ዝግጅት የተረከቡትን ችቦ ለተረካቢው ክልል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚያስረክቡ ጠቁመዋል።

በዕለቱ የሰርከስ ትርኢት እና የአትሌቲክስ ውድድር ተካሂዷል። በሥራ ኀላፊዎች መካከል አዝናኝ የመቶ ሜትር የሩጫ ውድድርም ተከናውኗል።

ዘጋቢ፡- ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የውኃ እጥረት ላሉባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች የሚውል ጀኔሬተር እና የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ድጋፍ አደረገች።
Next articleሜጋቢት 30/2016 ም.አ ቺርቤዋ ጋዚቲ