የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የውኃ እጥረት ላሉባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች የሚውል ጀኔሬተር እና የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ድጋፍ አደረገች።

20

ሰቆጣ: ሚያዚያ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የባሕር ዳር ደሴ የልማት ማስተባበሪያ ቢሮ በሰሜኑ ጦርነት እና በድርቁ ምክንያት የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት ላሉባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች የሚውል ጀኔሬተር እና የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ድጋፍ አድርጋለች። ድጋፋን ያስረከቡት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ደሴ የልማት ማስተባበሪያ ቢሮ የዋሽ ፕሮግራም ኮርድኔተር ደጀን ይግዛው የልማት ተራድኦ ድርጅቱ በሀገሪቱ ሦስት ክልሎች እንዲሁም በአማራ ክልል በኹሉም ዞኖች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ድጋፉም ሰባት የውኃ መሳቢያ ፓንፖች ከነሙሉ መገጣጠሚያቸው እንዲሁም ሦስት ትላልቅ ጀኔሬተሮችን ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የባሕር ዳር ደሴ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር የተደረገ ድጋፍ እንደኾነ አቶ ደጀን አስረድተዋል። ድጋፉ ትራንስፖርቱን ጨምሮ ከ29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል ብለዋል። በቀጣይም ቤተክርስትያኗ ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ አራት ወረዳዎች ለ45 ሺህ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የዋግ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ኃይሌ ወልዴ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የተመረጠ የማንጎ ዘር በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ደግፋለች ነው ያሉት። እንዲሁም 1 ሺህ 380 ኩንታል የፊኖ ዱቄት፣ 1 ሺህ 300 ሊትር ዘይት እና 50 ኩንታል ክክ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች እንደደገፈች ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለዋግ ሕዝብ ለምታደርገው ድጋፍ እና አጋርነት በልማት ማኅበሩ ስም አመሥግነዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ አብርሃም አሰፋ የተደረገው የሦስት ጀኔሬተር እና የሰባት ውኃ መሳቢያ ፓምፕ ከነመለዋወጫው ከ29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ገልጸዋል። ድጋፉም ለሰቆጣ ከተማ እና ለሰቆጣ ዙርያ ወረዳ የሚውል እንደኾነ የገለጹት አቶ አብርሃም ይህም ከ75 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ስለተደረገው ድጋፍ ምሥጋና ያቀረቡት መምሪያ ኀላፊው የውኃ መሳቢያ ጀኔሬተሮቹ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተገጣጥመው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የውኃ እና ኢነርጂ መምሪያው እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡-ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሠራር አስተዋወቀ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የኦሎምፒክ ችቦን ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አስረከበ።