
እንጅባራ ፡ ሚያዝያ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የለማ የጓሮ አትክልትን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አስጎብኝቷል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለከተማ ግብርና ተመራጭ እንደኾነ የሚነገርለትን “ቨርቲካል ፋርሚንግ” ቴክኖሎጂን በመተግበር ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች እና ለሥራ ኀላፊዎች ልምድ አጋርቷል።
የዩኒቨርሲቲው ምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ክንዴ ብርሃን (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የአካባቢው ማኅበረሰብ በውስን ቦታ የምግብ ፍላጎቱን እንዲሸፍን የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል። የግብርና፣ ምግብ እና የአየር ንብረት ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሀብታሙ አድማስ (ዶ.ር) ቴክኖሎጂው ኅብረተሰቡ ባለው ውስን መሬት የወዳደቁ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችን በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ “ቨርቲካል ፋርሚንግ” ቴክኖሎጂን ለመተግበር የሚያደርገውን ጥረት ዩኒቨርሲቲው ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾኑንም ዶክተር ሀብታሙ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አድማሱ ጌታሁን ቴክኖሎጂው ለከተማ ግብርና ተመራጭ በመኾኑ ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም ከጉብኝቱ ያገኙትን ዕውቀት እና ልምድ በአካባቢያቸው ለመተግበር ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የትምህርት ተቋማት ርዕሳነ መምህራን፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!