
አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር ያለውን የምግብ ብክነት ለማስወገድ እና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሦስት ሀገራዊ ስትራቴጂዎችን ከሚመለከታቸው የክልል የግብር ቢሮዎች፣ ከእንስሳት ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ይፋ አድርጓል።
ይፋ በተደረጉት ስትራቴጂዎች ላይም የግብርና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የመንግሥት እና የግል ተቋማት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ስትራቴጂዎችም የብሔራዊ የምግብ ደኅንነት እና ጥራት ለተቀዳሚ የግብርና ምርቶች ደኅንነት እንዲሁም ብሔራዊ የድህረ ምርት አያያዝ እና ሥርዓተ ምግብ ተኮር የምግብ ሥርዓት ስትራቴጂ ናቸው።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) አሁን ላይ የምግብ ሥርዓቱ ክፍተት ያለበት በመኾኑ የኅብረተሰቡ የተሰባጠረ የአመጋገብ ሁኔታ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ አይደለም ብለዋል፡፡
ዶክተር ግርማ ይፋ የተደረጉት ስትራቴጂዎች የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ አስረድተዋል።
ስትራቴጂዎች እንዲተገበሩ እና የምግብ ሥርዓት ሽግግርን በማሳለጥ ለውጦች እንዲመጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!