“የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

54

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማስፈተን ተማሪዎችን በበይነ መረብ የመመዝገብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የ6ኛ ክፍል ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል አቀፍ ደረጃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የ8ኛ ክፍልም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚወጣው አካሄድ መሠረት እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡ 7 ሺህ 543 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ አከናውነው የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊዋ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ እያካሄዱ ያሉት 5 ሺህ 421 ትምህርት ቤቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 133 ሺህ 184 ተማሪዎች በበይነ መረብ ምዝገባ መፈጸማቸውንም ገልጸዋል፡፡ 5 ሺህ 806 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ አካሂደው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናሉ ተብሎ ታስቦ እንደነበር ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ የመማር ማስተማር ሥራ እየተሠራባቸው እና ምዝገባ እየተካሄደባቸው ያሉ 4 ሺህ 155 ትምህርት ቤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 151 ሺህ 634 ተማሪዎች ተመዝግበዋል ነው የተባለው፡፡ የ6ኛ ክፍል እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ምዝገባ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ፈተናው በሁለት ዙር እንደሚሰጥ ያመላከቱት ምክትል ኀላፊዋ ቀድመው የተመዘገቡት ተማሪዎች ሰኔ/2016 ዓ.ም እንደሚፈተኑ ገልጸዋል፡፡ ዘግይተው ከተመዘገቡት መካከል ላይ ያቆራረጡ እና መማር ያለባቸውን ትምህርት በአግባቡ ያልተማሩ ተማሪዎች የሁለተኛ መፈተኛ ጊዜ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በየትኛው የመፈተኛ ጊዜ መፈተን እንደሚፈልጉ ለመወሰን ከተማሪዎች እና ከወላጆች ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ወቅቱ ለትምህርት ዘርፉ ፈታኝ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ ተማሪዎችን ማብቃት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የትውልድ ግንባታ ሥራ የሚቋረጥ አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በተለይም በ8ኛ ክፍል ፈተና የነበሩ ጉድለቶችን እና ጥንካሬዎችን መለየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጉደለቶችን ለማስተካከል ጥንካሬዎችንም ለማስቀጠል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተለያዬ ምክንያት የባከኑ ክፍለ ጊዜያትን የማካካስ ሥራ እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል፡፡ በተለይም የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና የሚወስዱት ለመጀመሪያ ጊዜ በመኾኑ መደናገጥ እንዳይኖር የሥነ ልቡና ሥራዎች እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የ8ኛ ክፍል ፈተና የሚዘጋጀው ከ8ኛ ክፍል መጽሐፍት ብቻ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎች በምን አይነት የትምህርት አይነቶች እንደሚዘጋጁ አስቀድሞ መነገሩንም ገልጸዋል፡፡ የ6ኛ ክፍል ፈተና እንዲዘጋጁ የሚጠበቀው ከ5ኛ ክፍል እና ከ6ኛ ክፍል ነው ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ለዚህ ዓመት ብቻ ከ6ኛ ክፍል ብቻ እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡ ይሄም የኾነው ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

በ2015 እና በ2016 ዓ.ም 14 ነጥብ 3 ሚሊዮን መጻሕፍት ማሳተማቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከታተሙት መጻሕፍት መካከል 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን መጻሕፍት ማሰራጨታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የመጽሐፍት ስርጭት የተሻለ መኾኑን እና በ2ኛ ደረጃ ላይ ግን እጥረቶች መኖራቸውን ነው ያነሱት፡፡ በቀጣይም የመጻሕፍት ሕትመቶች እንደሚኖሩም አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የማይሰጥ የትውልድ ግንባታ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ማንም አካል ቢኾን የልጆቹን መማር መደገፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ለልጆች የወላጆች እገዛ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለፈተና ዝግጅት እንዲያውሉ እገዛ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ መምህራን፣ የትምህርት መሪዎች እና ማኅበረሰቡ ለተማሪዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ።
Next articleየምግብ ብክነትን ማስወገድ እና ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ሦስት ሀገራዊ ስትራቴጂዎችን የግብርና ሚኒስቴር አስተዋወቀ፡፡