ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማካካሥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

23

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም በርካታ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማሩ ሥራ ተመልሰዋል፤ እየተመለሱ ነው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማካካስ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ የመማር ማስተማር ሥራ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ትምህርት እንደቀጠለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ሳይጀምሩ በቆዩ አካባቢዎች የእቅድ ክለሳ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲጀምር ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ሲያስተምሩ የነበሩ ትምህርት ቤቶችን የመከታተል እና የመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከፍተኛ የክልሉ መሪዎች የመማር ማስተማር ሥራውን ማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ የትምህርት ሴክተሩ ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የተቋረጡ ክፍለ ጊዜያትን የማካካስ ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ መምህራንም የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ተማሪዎች ለመማር ያሳዩት ተነሳሽነት እና ፍላጎት አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ድጋፍ እና ክትትሉ መቀጠሉንም አመላክተዋል፡፡

ምክትል ኀላፊዋ ለትምህርት ቤቶች ግብዓት የማቅረብ ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍትን ለክልሉ ማድረሱን የተናገሩት ምክትል ኀላፊዋ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጻሕፍት መሰራጨታቸውንም አንስተዋል፡፡ ማስተማር በሚችሉ እና አሁን እያስተማሩ ባሉ ትምህርት ቤቶች ለማድረስ ጥረት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ቀሪዎቹ መጻሕፍት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቢሮው የሚጠበቅበትን የግብዓት አቅርቦት ለማሟላት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በፀጥታ ሁኔታው ምክንያት በተፈጠረው ችግር በተሟላ መንገድ ተሠርቷል ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡

በቀሪ ጊዜያት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ እና ተማሪዎች ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት እንዲያሳልፉ ማድረግ ከወላጆች እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡ ቀሪውን ጊዜ ለንባብ እንዲሰጡ እና ለፈተና እንዲዘጋጁ ማድረግ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡ መምህራንም ቀሪ የትምህርት ምዕራፎችን መሸፈን እና ተማሪዎች በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲስመዘግቡ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች ማሟላት የሚገባቸው ደረጃ እንዳለ የተናገሩት ምክትል ኀላፊዋ ተማሪዎችም ከማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ ነገሮች ነጻ መኾን አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የመማር ማስተማር ሥራውን የሚረብሹ ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን አጥር መሠረት ተደርጎ ለንግድ ሥራዎች መስጠት ተማሪዎችን ለሱስ የሚጋዝቡ እንደሚኾኑ ነው የተናገሩት፡፡ ትምህርት ቤቶችን ከመሰል ችግሮች ነጻ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ብቻ ትኩረት እንዲሠጡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደሚሠራም ምክትል ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ከግንዛቤ ፈጠራው ባሻገር ትምህርት ቤቶችን ለደባል ሱስ ከሚጋብዙ እና ሊረብሹ ከሚችሉ ነገሮች ነጻ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት፡፡ መንግሥት ከሚያደርገው ቁጥጥር ባለፈ ማኅበረሰቡም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና አገልግሎቱ ፍትሐዊ እና ተደራሽ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
Next articleፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ።