
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመናዊ ዲጂታል የጤና መረጃ አሥተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት የጤና አገልግሎቱ ፍትሐዊ እና ተደራሽ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት የክልል ጤና ቢሮዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ባለፉት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር በተሠራው የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓትን የማዘመን ሥራ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የገለጹት በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ጤና መሪ ሥራ አሥፈፃሚ ገመቺስ መልካሙ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ ዶክተር ገመቺስ በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የመረጃ ጥራት ተደራሽነት እና አጠቃቀም ጉድለት በመቅረፍ የጤና አገልግሎት ዘርፉን ማሻሻል እና ተደራሽ ማድረግ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን የጤና መረጃ ጥራትን ለማሻሻል፣ የመረጃ አጠቃቀም ባህሪን ለማጎልበት እና መረጃን ዋቢ ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ አሠራርን ለማስረጽ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በዲጂታል መንገድ የሚተገበረው የጤና መረጃ ሥርዓት ሲስተም የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበት በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋማት ተደራሽ ይኾናሉም ነው የተባለው።
በመረጃ ቅብብሎሽ እና አጠቃቀም ላይ ያሉ መሠረታዊ ክፍተቶችን ለመፍታት ያግዛል የተባለው የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማዘመን ላይ ያተኮረው ውይይት ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ታውቋል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!