
ደሴ: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ክልላዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው። በንቅናቄ መድርኩ ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ከምሥራቅ አማራ ግብርና መምሪያ ኀላፊዎች እና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ባለፉት ዓመታት የምርት ውጤት እና በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ መክሯል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዞኑ በ2016/17 የመኸር ልማት ሥራ በዞኑ ከ430 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል እንደሚለማ ገልጸዋል። ያለው አንፃራዊ ሰላም በግብርና ዘርፍ የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንዳስቻለም ተናግረዋል። ከግብዓት አቅርቦት አኳያ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 339 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ማሰራጨት መቻሉን አቶ አሕመድ ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሸት በዞኑ 495 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል ምርት እንደሚሸፈን ተናግረዋል። ከዚህም 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በግብርናው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ያመረቱትን ምርት ለገበያ ማቅረብ ተቸግረዋል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው። ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የግብርና ሥራዎችን የማሳለጥ ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
በክልሉ በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሠራ መኾኑንም ቢሮ ኀላፊው አብራርተዋል። በተያዘው የምርት ዘመን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ለአማራ ክልል የመኸር ሥራን ለማገዝ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ግዢ የተፈፀመ ሲኾን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉንም ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!