
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ቶንሲል በጉሮሮ ቀኝ እና ግራ ክፍል በሚገኙ እጢዎች መመረዝ እና መጠቃት ምክንያት የሚመጣ ሕመም ነው፡፡ እነዚህ እጢዎች የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት አካል ናቸው፡፡ እጢዎቹ በጉሮሮ እና በአካባቢው ሰርገው የገቡ በሽታ አምጭ ተህዋስያንን የመከላከል ሥራ በመሥራትም ሁነኛ ሚና አላቸው።
የሕመሙ ዋና መንስኤ ባክቴሪያ እና ቫይረሶች እንደኾኑ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባወጣው መረጃ ገልጿል፡፡ ይህ ሕመም አንዳንድ ጊዜም በፈንገስ አማካኝነት ሊከሰት እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው የቶንሲል ሕመም በባክቴሪያ ከሚከሰተው አንጻር መጠኑ እጅግ ከፍ ያለ እንደኾነም ነው የሕክምና ባለሙያዎች የሚገልጹት፡፡
በሽታው በማሳል እና በማስነጠስ ከአንድ ግለሰብ ወደ ሌላ ግለሰብ እንደሚያስፋፉም ያስገነዝባሉ። በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰተው የቶንሲል መጠኑ ዝቅ ያለ ቢኾንም አፋጣኝ የሕክምና ትኩረት ካላገኘ መወሳሰብ ፈጥሮ በሰዎች ላይ ትርጉም ያለው ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ነው የሚገለጸው፡፡
የቶንሲል ምልክቶችም፡-
👉 የጉሮሮ መቁሰል እና ህመም
👉 የቀላና ያበጠ ቶንሲል
👉 በምንመገብበት ወቅት የህመም ሥሜት
👉 ትኩሳት መኖር
👉 ራስ ምታት
👉 በጆሮ እና አካባቢው የሚፈጠር ህመም
👉 ለመተንፈስ መቸገር
👉 ከፍተኛ የድካም ስሜት
👉 እንቅልፍ ማጣት
👉 ብርድ ብርድ ማለት እና መሰል ምልክቶች ይታያሉ
ለቶንሲል አጋላጭ መክንያቶች፡-
👉 ከእድሜ ወሰን አኳያ በተለይም በሕጻናት ላይ በሽታው የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ነው
👉 የሰውነት የመከላከል አቅም መዳከም
👉 ማጨስ
👉 ከፋብሪካዎች ወይም ከከሌሎች ምንጮች ወደ ከባቢ አየሩ የሚረጩ አደገኛ ኬሚካሎች
የቶንሲል ህመምን ለማከም የቤት ውስጥ የህክምና መንገዶች፡-
👉 እረፍት ማድረግ
👉 የፈሳሽ መጠንን ማብዛት
👉 ለብ ያለ ውኃ ከማር ጋር ወይም ያለማር መጠጣት
👉 ቡና እና ካፊን ከያዙ መጠጦች መታቀብ
👉 ውኃን ከጨው ጋር ቀላቅሎ ሳይውጡት ጉሮሮ አካባቢ ማመላለስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!