የሰሜኑ ጦርነት በትምህርት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመመለስ እየተሠራ ነው።

44

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ውድመት ከደረሰባቸው የአማራ ክልል የማኅበራዊ ተቋማት መካከል የትምህርት ዘርፉ አንዱ ነው። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የዕቅድ እና ሃብት ማፈላለግ ዳይሬክተር ምሥጋናው አማረ በጦርነቱ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

ከጦርነቱ በኋላ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማልማት እና ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ምሥጋናው እስካሁን 225 ትምህርት ቤቶች የተጠገኑ እና የተገነቡ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህም ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር የ45 ትምህርት ቤቶችን ግንባታ እያጠናቀቀ መኾኑንም አመላክተዋል።

በተለያዩ አካላት ርብርብ በየዓመቱ 200 ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ ቢኖርም በዕቅዱ መሰረት አለመከናወኑን አቶ ምሥጋናው አሳውቀዋል። ለረጂ አካላት ተጨማሪ ጥያቄ ለማቅረብ የተጀመሩትን ግንባታዎች በወቅቱ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና ውድመት መልሶ ለመገንባት በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት በ2014 ዓ.ም በአማራ ክልል በደንብ ቁጥር 198/2014 ተቋቁሟል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አሥኪያጅ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ጦርነቱ ያደረሰው ውድመት ተጠንቶ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ድረስ 2 ሺህ 935 የትምህርት ተቋማት ከቀላል እስከ ከባድ ውድመት የደረሰባቸው መኾኑን ገልጸዋል።

ውድመቱን መልሶ ለመጠገን ከአማራ ክልል፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ ልማቱ መጀመሩን የጠቀሱት ዶክተር አባተ ከወደመው ሃብት ጋር ሲነጻጸር የተገኘው ድጋፍ አነስተኛ በመኾኑ በታቀደው ልክ መፈጸም አለመቻሉን አመላክተዋል።

በክልሉ ለጠቅላላ መልሶ ልማት ከተገኘው ድጋፍ ውስጥ 332 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ 22 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እና 4 ኮሌጆችን ለመደገፍ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን እና የ105ቱ ግንባታ መጠናቀቁን ነው ዶክተር አባተ የገለጹት።

ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍም በ20 ወረዳዎች ላይ 220 የትምህርት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መኾኑን ጠቅሰዋል። የመቀመጫ ወንበር እና ኮምፒዩተሮችን የማሟላት ሥራም እየተሠራ ነው። የትምህርት ቤቶቹ ግንባታዎች ዘመናዊ እና ጥራታቸውን የጠበቁ መኾናቸውን ነው ዶክተር አባተ የገለጹት። የአንድ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና የአንድ የሬዲዮ ትምህርት ማሰራጫ ጥገናም ከትምህርት ቢሮ ጋር በትብብር እየተሠራ ነው።

በአማራ ክልል በ94 ወረዳዎች የደረሰው ውድመት ሰፊ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር አባተ በሌሎች ዘርፎች ላይም ከፍተኛ ውድመት በመኖሩ እና የሃብት ውስንነት ስላለ በፍጥነት ማገገም አለመቻሉን ነው የተናገሩት።

75 የገቢ ምንጭ ማሠባሠቢያ ስልቶች ታቅደው የነበረ መኾኑን የጠቀሱት ሥራ አሥኪያጁ በክልሉ የተከሰተው ግጭት ባያደናቅፍ ኖሮ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገንዘብ በመሠብሠብ ተጨማሪ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችንም ለመሥራት ታቅዶ እንደነበር ጠቁመዋል።

ዶክተር አባተ ከክልሉ እና ከፌዴራሉ መንግሥት በተጨማሪ ከዓለም ባንክ እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ)፣ ከዲያስፖራው፣ ከባለሃብቶች፣ ከሃይማኖት ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና ከእያንዳንዱ ዜጋ አስተዋጽኦ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በቀጣይም ከኢምባሲዎች ጭምር በመጠየቅ መልሶ የመገንባት እና የማልማቱን ሥራ እንደሚቀጥል የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ ኅብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሳይንስ ሙዚየም እየታየ ያለው የ’ስታርት አፕ’ ኢትዮጵያ አውደርዕይ በዘርፉ ያሉ ተሳታፊዎችን ተምኔት፣ የፈጠራ ምናብ ስፋት ብሎም ችሎታ ማሳያዎች ቀርበውበታል። ሁላችሁም አውደ ርዕዩን በመመልከት ከተሳታፊዎቹ ጋር እንድትወያዩ እጋብዛለሁ።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶር.)
Next articleበሚገባው መጠን ካልታከመ ውስብስብ የጤና እክል የሚያስከትለው የቶንሲል ሕመም