
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማ መሥተዳደር ውይይት ተካሂዷል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኤልያስ አበበ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት 112ኛ ክፍለጦር የአየር ወለድ እና ኮማንዶ አዛዥ ኮሎኔል አሠፋ አየለ ለተከታታይ በርካታ ቀናት የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሲያወያዩ ቆይተዋል።
በዛሬው እለት በአጣዬ ከተማ መሥተዳደር ከሦስቱም ቀበሌዎች ከተገኙ ወጣቶች ጋር በከተማዋ እና በቀጣናው የሰላም ጉዳይ ላይ አወያይተዋል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት 112ኛ ክፍለጦር የአየር ወለድ እና ኮማንዶ አዛዥ ኮሎኔል አሠፋ አየለ እንደጠቀሱት ወጣቱ ትኩስ እና ቀልጣፋ ኀይል ነው፤ ይሄ ኀይል ደግሞ የተሰማራበትን ጉዳይ ለማሳካት ፈጣን ነው፤ ምን አልባትም ለበጎ ነገር ኀይሉን ካልተጠቀምነው ሀገርን ዋጋ የሚያስከፍል ኀይል ነው።
ከዚህ ኀይል ጋር ደግሞ “ለሰላም” ተቀራርበን እንሠራለን ያሉት ኮሎኔል አሰፋ ከጥፋት ኀይል በመራቅ እና ለፀጥታ መዋቅር ድጋፍ በማድረግ ቀጣናውን ሰላም በማድረግ ለሚደረገው ጥረት ወጣቶች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኤልያስ አበበ በአጣዬ እና አካባቢው ያለ ሰው የኾነ ብቻም ሳይኾን እንሰሳት ሁሉ ሞተዋል፤ ቆስለዋል፣ ሀብት እና ንብረት መውደሙ የሚካድ አይደለም፤ ከዚህ በኋላ በዛው እንዲበቃ መሥራት አለበት ብለዋል።
ሰው ለሰው ሁሉ ሩህሩህ በመኾን ሊያዝን ይገባል፤ ወዶ ባልተፈጠረበት ብሔሩ መፈለግ የለበትም፤ መገፋትም የለበትም፤ በዘረኝነት እሳቤ ያሉ የተሳሳተ እሳቤ ነው ከዚህ መራቅ ይገባል ብለዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ እንደጠቀሱት ደግሞ ለአጣዬ ከተማ ሰላም መሥራት እና ሰላም መሆን ለሰንበቴም ብቻ ሳይሆን ለይፋት ቀጣና ትልቅ ትርጉም አለው፤ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጋር እየተሠራ ነው፤ ይህንንም ተግባር አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ተባባሪ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን የተሄደበት መንገድ ስህተት ነው፤ በስህተታችንም ደግሞ እናቶቻችንን ለሀዘን፣ አዛውቶችን ደግሞ ለእንግልት ዳርገናል። ይሄ ሁሉ የኾነው በሰዎች ድምር ጥፋት ነው ያሉት አቶ መካሻ ያለፈው ሁሉ አልፏል ለቀጣዩ አጥብቀን መሥራት መቻል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ያሉት።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ወጣቶችም ሰላም የሚጠላ ሕዝብ አለ ብለን አናስብም፤ ሁሉም ሰላም ይፈልጋል፤ በሚፈልገው ልክ ግን የድርሻውን ባለመወጣቱ ለዚህ ተዳርገናል ነው ያሉት። ለሚደረጉ ጥፋቶች ተዋናዮቹን መንግሥት እንዲያጠራ እና እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀው ለሰላም እና ለአንድነት መሥራት ከሚችሉ ሁሉ ጋር እንሠራለን በማለት ማረጋገጣቸውን ከኤፍራታና ግድም ወረዳ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መመጃ ያመለክታል።
“እኛ የአጣዬ ልጆች ኾነን በአጣዬ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚደረጉባት፣ በርካታ አውቶብሶች የሚጎርፉባት፣ የንግድ እንቅስቃሴዋ ለሁሉም ምቹ የሆነችዋን ከተማ እንናፍቃታለን” ያሉት ወጣቶቹ መንግሥት ቀርቦ ከሕዝቡ ጋር ከሠራ ወደነበረበት ለመመለስ እሩቅ አይደለም፤ ለዚህም ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ሃሳባቸው ሰጥተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!