በክልሉ የተካሄዱ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው ሕዝብ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምሥጋና አቀረበ፡፡

43

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሳምንቱ የተከናወኑ የድጋፍ ሰልፎች እና የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም መጠናቀቃቸውን ፖሊስ አስታውቋል። በሳምንቱ በአማራ ክልል ከተከናወኑ ሁነቶች ውስጥ የድጋፍ ሰልፎች እና የዒድ አልፈጥር በዓል ይጠቀሳሉ። ሁነቶቹ በሰላም መጠናቀቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

በኮሚሽኑ የሚዲያ ዋና ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ እንዳሉት በያዝነው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በወልዲያ፣ ደሴ ፣ኮምቦልቻ ፣ደብረታቦር እና ሰሜን ጎንደር ዞን የድጋፍ ሰልፎች ተከናውነዋል፡፡ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም ደግሞ 1ሺህ 445ኛ የዒድ አልፈጥር በዓል ተከብሯል።

የድጋፍ ሰልፎች እና የዒድ አልፈጥር በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ የአማራ ክልል እና የፌዴራል የጸጥታ አባላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል። በተሠራው ሥራም ሰልፎቹ እና በዓሉም ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቅቋል ብለዋል። በተለይም ደግሞ የዒድ አልፈጥር በዓል ሰላም ኾኖ እንዲጠናቀቅ የእምነቱ ተከታይ ወጣት አደረጃጀቶች ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።

በበዓሉ የነበረው መከባበር እና አንድነት በቀጣይ በመደበኛ ጊዜያትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስረድተዋል። ሰልፎቹ እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረጉ ሁሉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምሥጋና አቅርቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከዜ የብረት ድልድይ ሥራ አፈጻጸም ከ87 በመቶ በላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡
Next articleለአጣዬ ከተማ እና አካባቢው ሰላም መኾን ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።