የተከዜ የብረት ድልድይ ሥራ አፈጻጸም ከ87 በመቶ በላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡

24

ሰቆጣ: ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ በተከዜ ወንዝ ላይ የሚከናወነው የብረት ድልድይ ሥራ አፈጻጸም ከ87 በመቶ በላይ መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ደጉ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከዝቋላ ወረዳ እና ከብሔረሰብ ዞኑ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ ሥራ ጥር 29 2016 ዓ.ም መጀመሩ ተመላክቷል፡፡ ሥራው 87 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ በቀሪ 15 ቀናት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሥራ አሥኪያጁ እንደገለጹት የብረት ድልድዩን ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ከ256 ሚለየን ብር በላይ በጅቷል፡፡ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ግንባታውን እያከናወነ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ የአማራ ክልል ልህቀት ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ደግሞ ግንባታውን ከነዲዛይኑ እያመከረ ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በድልድዩ የሥራ ሂደት ደለል ለማውጣት 14 ሜትር ጥልቀት መቆፈር እና መሰል ፈተናዎችን ማለፍ ቀላል እንዳልነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ ችግሮችን ተቋቁመው የግንባታ ሥራው ወደ መጠናቀቁ በመድረሱ መደሰታቸውን አመላክተዋል፡፡ የሁለቱ ወረዳዎች ነዋሪዎች፣ የወረዳዎቹ እና የዞን መሪዎች የጸጥታ ሁኔታውን በመጠበቅ ሥራውን በመደገፍ ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል የልህቀት ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን እና የተከዜ ፕሮጀክት ተጠሪ መሐንዲስ ዳኘው ሰማኸኝ ሥራው በ73 ቀናት ውስጥ 87 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡ የግንባታ ሥራውን ለማጠናቀቅ የአራት ወራት እቅድ መያዙን ያስታወሱት ተጠሪ መሐንዲሱ በእቅድ ከተያዘው ጊዜ በፊት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በምክትል አስተዳዳሪ ማዕረግ የመንገድ መምሪያ ኀላፊ ፀጋው እሸቴ የተከዜ የብረት ድልድይ ጉዳይ ከአራት ዓመታት በላይ የሕዝብ ጥያቄ ኾኖ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ግንባታውን ማስጀመራቸውን አመላክተዋል፡፡ የፌደራል መንግሥት የድልድዩን የንጣፍ ብረት እያጓጓዘ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የድልድዩ መሠራት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሁሉን አቀፍ ሚናው የጎላ መኾኑን ያነሱት አቶ ፀጋው ቀሪ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
Next articleበክልሉ የተካሄዱ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው ሕዝብ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምሥጋና አቀረበ፡፡