የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡

22

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማጠናከሪያ ትምህርት ሲማሩ ያገኘናቸው በአላማጣ ከተማ የታዳጊዋ ኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ቁጥር መብዛት ጫና አሳድሮባቸው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

አሁን ዩኒቨርሲቲው እያደረገላቸው ያለው ተጨማሪ ድጋፍ ከመምህሮቻቸው ድጋፍ እና ከራሳቸው ጥረት ጋር ተዳምሮ ስኬታማ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ነግረውናል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት አሥተባባሪ አሳምን እምቢአለ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በሰሜን ወሎ ዞን በተመረጡ አምስት ማዕከላት የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የማጠናከሪያ ትምህርቱ በአምስት የትምህርት ዓይነቶች በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ለ2 ሺህ 200 ተማሪዎች እየተሠጠ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ዶክተር አሳምን በሥራው ላይ 102 መምህራን የሚሳተፉበት እና ለሁለት ወራት የሚቆየው ይህ የትምህርት ሂደት ቅዳሜ እና እሁድ የሚከወን መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ለማስተማር ከተመረጡት የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች በተጨማሪ የሥነ ልቦና ሥልጠና እንደሚሰጥ ነው ዶክተር አሳምን ያስረዱት። የትምህርት ኘሮግራሙ አላማጣ ከተማ፣ ራያ አላማጣ ወረዳ፣ ቆቦ ከተማ እና ጉባላፍቶ ወረዳን ያቀፈ ኘሮግራም መኾኑን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአይ.ኦ.ቲ
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡