አይ.ኦ.ቲ

61

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰዎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መረጃን እንደሚለዋወጡት ሁሉ በቤታችንም ኾነ በሥራ ቦታችን የምንገለገልባቸው ቁሳቁሶች መረጃን በመለዋወጥ መግባባት እና ተግባራትን ማከናወን የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ የቁሶች በበይነ መረብ መተሳሰር (አይ.ኦ.ቲ) ይባላል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ስማርት የሆነ ከባቢን ለመፍጠር ወሳኝ ሚናን የሚጫወት ነው፡፡ አይ.ኦ.ቲን በመጠቀም ሰዎች ከሰዎች ወይም ሰዎች ከማሽኖች ጋር ተግባቦት መፈጸም ሳይጠበቅባቸው ቁሶች እርስ በራሳቸው የሚኖራቸው የመረጃ ልውውጥ ለውሳኔ እንዲያግዝ ኾኖ ወደ መረጃ ቋት መተላለፍ ይችላል፡፡

በኾነ አጋጣሚ የኤሌክትሪክ ምድጃ ላይ የኾነ ነገር ጥደን፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ለኩሰን ወይም ቴሌቪዥን ከፍተን መዝጋት እንዳለብን ረስተን ሩቅ ቦታ ብንሄድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀላል እና ከባድ የሚባሉ አደጋዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን አይ.ኦ.ቲ እንዲህ ዓይነት ቀላል ችግሮችን ብቻ ሳይኾን የተለያዩ ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ አደጋዎችን ማስወገድ ይችላል፡፡

በቤታችን ውስጥ ያሉ ቁሳቁሶችን በሴንሰሮች አማካኝነት በማስተሳሰር ያሉበትን ሁኔታ ከርቀት ኾነን መቆጣጠር እና ማዘዝ እንችላለን፡፡ በቁሳቁሶች መካከል የሚኖረው የግንኙነት መረጃ በበይነ መረብ አማካኝነት ክላውድ ላይ የሚቀመጥበት ሥርዓት አለ፡፡ ክላውድ ላይ የተቀመጠውን መረጃ በመመልከት ስልካችን ላይ ትእዛዝ ማስተላለፍ እንችላለን፡፡ የአይ.ኦ.ቲ ቁሶች የሴንሰሮችን መረጃ ወደ ክላውድ የሚያስተላልፉት በአይ.ኦ.ቲ ጌትዌዎች (ከኢንተርኔት ጋር የመገናኛ በር) በኩል ነው፡፡

የአይ.ኦ.ቲ ቴክኖሎጂን በቤታችን፣ በከተሞች፣ በሥራ ቦታ፣ በትላልቅ ድርጅቶች እና በሌሎችም ቦታዎች ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ የአይ.ኦ.ቲ መገልገያዎች በአብዛኛው ያለሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት በራሳቸው ተግባራትን የሚያከናውኑ ሲኾን የሰዎች ጣልቃ ገብነት መረጃን ለማግኘት አሊያም ትዕዛዛትን ለመስጠት ብቻ ነው፡፡

አይ.ኦ.ቲ ስንል ሁለት መሠረታዊ ቁሶችን በዋናነት እናነሳለን እነዚህም እንደ ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ እና የኤሌክትሪክ ማብሰያ የመሳሰሉ መገልገያ ቁሳቁሶቻችን እና ሴንሰሮች ናቸው፡፡ ሴንሰሮቹ የቁሳቁሶችን የሙቀት፣ የእርጥበት እና የብርሃን መጠን በመረዳት መረጃን ወደ ክላውድ በመላክ ከርቀት ኾነን ውሳኔ እንድንሰጥ ያግዛሉ፡፡ ስልካችን ላይ ኾነን ትዕዛዝ ለመስጠት ቁሳቁሶች በሚኖራቸው ቅርበት እና ርቀት በብሉቱዝ፣ ኢንፍራሬድ አሊያም በኢንተርኔት ሊገናኙ ይገባቸዋል፡፡

የበለጠ ምርታማ ለመኾን፣ ገንዘብ እና ጊዜን ለመቆጠብ፣ የሰራተኛን ምርታማነት ለማሳደግ እና ተጨማሪ ገቢን ለማግኘት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው አይ.ኦ.ቲ፡፡ በተለያዩ ቁሳቁሶች መካከል የሚደረገው የመረጃ ዓይነት እና ብዛት ከፍተኛ ከመኾኑ አንጻር ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ የመኾን እድል ከፍተኛ መኾን፣ የአይ.ኦ.ቲ መገልገያዎች ብዙ ከመኾናቸው አንጻር ውስብስብ የኾነ የማሥተዳደር ሥራ መጠየቁ እና ወጥ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ባለመኖሩ ምክንያት አንዱ መገልገያ ከሌላው ጋር ለመግባባት ያለመስማማት ችግር (ኮምፓቴቢሊቴ ፕሮብሌም) በዚህ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚነሱ ፈታኝ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

ምንጭ
https://www.techtarget.com/…/def…/Internet-of-Things-IoT

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከባለፈው የምርት ዘመን በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየወልድያ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡