
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምርታማነት እድገት ማነቆ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል። የ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን የሰብል ልማት ፓኬጅ የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል። በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ አየተሠራ ይገኛል።
ባለፈው የምርት ዘመን ከተገኘው ምርት በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። አማካይ ምርታማነቱን በሄክታር ወደ 32 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራም ነው። ዶክተር ድረስ እንዳሉት በምርት ዘመኑ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጅዎችን እና ግብዓትን በሙሉ ፓኬጅ ለመጠቀም እንዲኹም ለምርታማነት እድገት ማነቆ በኾኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ግብርናው የሉዓላዊነት መገለጫ እና ሰላምን ማረጋገጫ መንገድ መኾኑን ኀላፊው አንስተዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች እና በየትኛውም ተቋም ላይ የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። አርሶ አደሩም የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ እንዲተገብር አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በምርት ዘመኑ የምግብ ፍላጎትን ማሳካት፣ በክልሉ እየተስፋፉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ በቂ ግብዓት ማሟላት እና የኤክስፖርት ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ለምርት መቀነስ ምክንያት የኾኑ የሰብል ተባይ እና በሽታዎች መከላከል ላይ እንደሚሠራ ነው ያስገነዘቡት። የአፈር አሲዳማነትን ማከም፣ የጥቁር አፈር ፓኬጅን ተግባራዊ ማድረግ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን የማሻሻል ሥራም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል።
በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ ምህረቱ ተስፋየ እንዳሉት በ2016/17 የምርት ዘመን በቂ ግብዓት እየቀረበ በመኾኑ ምርታማነትን ለመጨመር የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ለምነትን ማሻሻል እና የምርጥ ዘር ብዜት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። አሁን ላይ እንደ በቆሎ የመሳሰሉ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የግብዓት ሥርጭት መጀመሩንም ገልጸዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ በሪሁን እውነቱ እንደገለጹልን በ2015/16 የምርት ዘመን በነበረው የማዳበሪያ እጥረት፣ የተለያዩ ተባዮች እና በሽታዎች ምክንያት የታቀደውን ምርት ማሳካት አልተቻለም።
በ2016/17 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለማሻሻል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቀድሞ ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀመጡ ፓኬጆችን እና ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠናም በምርት ዘመኑ ክልሉ ለማግኘት ያቀደውን እቅድ ለማሳካት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!