
ደሴ: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ድምፃቸው ለዳውዶና አከባቢው ብሎም ለደሴ ከተማ ነዋሪ አዲስ አይደለም። ለአምስት አስርት ዓመታት የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጆሮ በቀን አምስት ግዜ ሲያንኳኳ ኑሯል።
በዳውዶ መስጂድ ከ50 ዓመታት በላይ አዛን ሲያደርጉ የኖሩ ሙአዚን ናቸው ሼህ መሐመድ ከማል። 50 ዓመታት በላይ ሳያቋርጡ፤ የአምስቱን የሰላት ወቅቶች ሰዓት ሳያዛንፉ ሙዕሚኑን ተጣርተዋል። በዚህ ሁሉ ዓመት ውስጥ የመዛል እና የመታከት ስሜት አልታየባቸውም።
የወቅቶች መፈራረቅ እንደ ሰርግ እና ሀዘን ያሉ የህይወት ክስተቶች አዛን ከማድረግ አልከለከላቸውም። ዶፍ ዝናብ ቢዘንብ ጥላቸውን ዘርግተው ይመጣሉ እንጂ አይቀሩም። አዛን ለማድረግ ለሊት ከጅብ ጋር እየተጋፉ ነው ወደ መስጂድ የሚሄዱት። ነገር ግን ጅቦቹ ከመሸኘት በስተቀር አንድም ቀን ተተናኩለዋቸው እንደማያውቁ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ነግረውናል።
ወደ ዳውዶ መስጅድ መጀመሪያ ሲመጡ ለሃይማኖታዊ አስተምህሮ የነበረ ቢኾንም በሰዎች ምርጫ ሙአዚን ሊኾኑ ችለዋል። ‘አዛን ሳደርግ ልዮ ደስታ ይሰማኛል!’ ይላሉ። በቅርብ የሚያውቋቸውም ሼህ መሐመድ ከማል ለአዛን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጡ እና ይህ የሙአዚንነት ተሰጥኦ ከአሏህ የተሰጣቸው በመኾኑ በብርታት ዛሬ ላይ መድረሳቸውን ይገልጻሉ።
ከሙአዚንነቱ ባሻገር እጅግ በርካታ ሰዎች ከሼህ መሐመድ ከማል ስር ሁነው ሃይማኖታዊ ትምህርት ተከታትለዋል። ያስተማሯቸው ልጆች በተለያዩ ዓለማት ቢበተኑም ሲመጡ ግን እግሮቻቸው የሚፈጥኑት ወደ ሼህ መሐመድ ከማል ዘንድ ነው። “ባቀራኋቸው ልጆች ምክንያት የበርካታ የዓለም ሀገራትን ስም አውቄያለሁ” ይላሉ።
ሰውን በዕድሜ፣ በዘር እና በሃይማኖት ነጣጥለው አይመለከቱም። ሁሉም ሰው በርሳቸው ዓይን እኩል ነው። ይህ ባህሪያቸው በጊዜ የማይለወጥ፣ በዘመን ተገፍቶ የማይንሸራተት መኾኑንም የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። በዚህ ምክንያትም በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ሰው ለመኾን ችለዋል።
ይህ ትውልድ ከሼህ መሐመድ ከማል በዕምነት መጠንከርን፣ ፍቅርን እና በጎ ማሰብን ሊማር እንደሚገባም የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!