የዒድ አልፈጥር በዓል ገጽታ በዓለም ዙሪያ

56

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዒድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዷን ወር ፆም መፍቻ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ የተወሰኑትን ሀገራት የዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር እንመልከት፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዒድ አልፈጥርን በተክቢር እና ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በአደባባይ እና በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ያከብራሉ፡፡

በዒድ አልፈጥር በሥራ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተለያዩ ቤተ ዘመዶች ተሠባሥበው በዓሉን በጋራ ያከብራሉ፡፡ በዒድ አልፈጥር አንድም ሙስሊም አጥቶ እና ከፍቶት እንዳይውል በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ጥረት ይደረጋል፡፡ ለዚህም ሲባል ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ ለማሠባሠብ ዘካተል ፊጥር ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ የአፍጥር መርሐ ግብሮች የሚከናወንባቸው አደባባዮች የክርስትና እና ሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ዝግጅቱ የሚካሄድበትን ቦታ በጋራ ኾነው ሲያጸዱ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ መባባል፣ ስጦታዎችን መለዋወጥ እና እንግዶችን ጠርቶ በቤት ውስጥ መጋበዝ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የዒድ አልፈጥር አከባበር መለያዎች ናቸው፡፡

አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ እስልምናን ቀድመው ከተቀበሉ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በሞሮኮ በዒድ አልፈጥር በዓል ጠዋት ላይ ወንዶች ከመስጅድ ሲመለሱ ሴቶች ያዘጋጁትን “ባንጋህሪር” እና “መልዊ” የተባሉ ባሕላዊ ምግቦችን ቁርስ ላይ እየቀማመሱ ሀሴት ማድረግን ይጀምራሉ፡፡ ወዳጅ ዘመድ ይጠይቃሉ፣ ድሆችን ይጎበኛሉ፣ በሆስፒታል እና በሕግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችም በቀኑ እንኳን አደረሳችሁ ይባላሉ፡፡ በበዓሉ እንደ አብዛኛው የዓለም ሀገራት ስጦታ መለዋወጥ በሞሮኮ የተለመደ አይደለም፡፡

ቱኒዝያውያን የዒድ አልፈጥር በዓልን “ኢዱል ፊትሪን” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የሀገሪቱን ሕዝብ 98 በመቶ የሚሸፍኑት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዒድ አልፈጥርን በልዩ ሁኔታ ክዋኔዎች ያከብሩታል፡፡ “ካክ” የተሰኘ የኬክ ዓይነት እና “ባክላዋ” የሚባል ልዩ ብስኩት የዒድ አልፈጥር በዓል ልዩ እና ተወዳጅ ምግቦች ናቸው፡፡

በሕንድ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ ሕንዳውያን ሙስሊሞች የዒድ አልፈጥር በዓልን ለማክበር ከቤታቸው ወጥተው በአደባባይ ተሠባሥበው በጋራ ለአሏህ ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ ወደ አደባባይ ለሰላት ከመውጣታቸው በፊት ግን ‹‹ሽር ኩመራ›› የተሰኘ ምግብ ከጣፋጭ ነገሮች እና ከሩዝ ከበዓሉ በፊት ባለው ምሽት ይዘጋጃል፡፡ በዒድ አልፈጥር ጠዋት ይህን ምግብ ተሠባሥበው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀምሳሉ፡፡ ሕንዳውያን ሙስሊም ሴቶች እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን በሂና በማስዋብ በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው ያሳልፋሉ፡፡ በዒድ አልፈጥር ስጦታዎችን መለዋወጥ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለወዳጅ ዘመድ ማስተላለፍ ለሕንዳውያን ሙስሊሞች የተለመደ ነው፡፡

በቱርክ ዒድ አልፈጥርን “ራመዳን ባይራም” ይሉታል፡፡ ቱርካውያን ሙስሊሞች በዒድ አልፈጥር በዓል ወደ መቃብር ቦታዎች በመሄድ ከዚህ ዓለም ያለፉትን ሰዎች የእረፍት ቦታ በአበባ በማስጌጥ በጸሎት ያስባሉ፡፡ ሕፃናት ወደ ጎረቤቶቻቸው በመሄድ እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ፡፡ ጣፋጭ ነገሮችን እና ገንዘብም ይቀበላሉ፡፡

የዘንድሮው የዒድ አልፈጥር በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋዛ፣ ሱዳን እና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የተነሳ ዒድ የወትሮውን ያክል አከባበር አልታየበትም እየተባለ ነው፡፡ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ሙሳ ፋኪ እና ሌሎች የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዒድ አልፈጥርን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ዓለም ከስጋት ትድን ዘንድ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡ ሮይተርስ፣ ቢቢሲ እና አልጀዚራን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል

ዒድ ሙባረክ!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን በወደድን ጊዜ ፈጣሪ በእዝነት ዐይኑ ያየናል”
Next articleየሁለቱ ዒድ እውነታዎች፡፡