“ሰላምን በወደድን ጊዜ ፈጣሪ በእዝነት ዐይኑ ያየናል”

27

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ፈጣሪ ትዕዛዛቱን የሚያከብሩለትን፣ በቃሉ የሚኖሩለትን፣ መልካሙን ነገር የሚያደርጉለትን ይወዳቸዋል፤ ይሳሳላቸዋል፤ ስለ መልካም ሥራቸው ሰው ያልመረመረውን፤ የሰው ልቡና ያላሰበውን ዋጋ ይከፍላቸዋል፡፡ ሁልጊዜም በእዝነት ዐይኑ ይመለከታቸዋል፡፡
ትዕዛዛቱን የሚያከብሩትን ያከብራቸዋል፤ ከፍ ከፍም ያደርገዋቸዋል፡፡ ትዕዛዛቱን በማያከብሩት ላይ ግን ቁጣውን ያዝንባቸዋልይላሉ፡፡ የሰው ልጆች ለአምላካቸው ተገዢነታቸውን ለማሳየት ስጋቸውን እያደከሙ፣ ነብሳቸውን እያበረቱ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ ቃሉን ይፈጽማሉ፡፡ ሙስሊሞች ከአምላካቸው የሚገናኙበትን ታላቁን ጾም ረመዷንን ይጾማሉ፡፡

ረመዷን በደረሰ ጊዜ እግሮች ይጾማሉ፣ አቅጣጫቸውን ወደ ፈጣሪ ቤት ወደ መስጅድ ያደርጋሉ፣ በተመረጠው ቦታ ይቆማሉ፣ ዐይኖችም ይጾማሉ፣ መጥፎውን ከማየት ይታቀባሉ፣ የፈጣሪ ቃልን ያስታውላሉ፣ ቁርዓንን ያነብባሉ፤ ጆሮዎች መልካሙን ነገር ለመስማት ያዘነብላሉ፣ የፈጣሪን የምስጋና ቃል ይሰማሉ፣ ከመስጅድ የሚወጣውን የአዛን ድምጽ ያዳምጣሉ፤ ልቦች ፈጣሪያቸውን አብዝተው ያስባሉ፣ አንደበቶች ከመጥፎ ንግግር ይታቀባሉ፣ እጆችም ለመስጠት ይዘረጋሉ፡፡

በረመዷን ደግነት ይደረጋል፣ የፈጣሪ ነገር አብዝቶ ይታሰባል፡፡ በዚህ ወር ሙስሊሞች ከምግብ ተከልክለው ፈጣሪያቸውን አብዝተው ያስባሉ፣ ምድርን ሰላም እና ፍቅር እንዲሰጣት፣ ባለፉ ጊዜ ነፍሳቸውን በጀነት እንዲቀበላት አብዝተው ዱዓ ያደርጋሉ፤ ጀነትን ለመውረስ ይራባሉ፤ በጀነት ለመኖር ይጠማሉ፡፡
በታላቁ ወር ካላቸው ላይ እየከፈሉ የተራበን ያበላሉ፣ የተጠማን ያጠጣሉ፣ የታረዘን ያለብሳሉ፣ መጠጊያ ያጣውን ያስጠልላሉ፤ በፍቅር ተቀብለው ያስጠጋሉ፤ ሲጾም ውሎ ማፍጠሪያ ያጣውን ያስፈጥራሉ፤ ፈጣሪ የሚያዝዘውን መልካሙን ነገር ሁሉ ለማድረግ ይፋጠናሉ፡፡ በረመዷን መልካሙን ማድረግ ከፍ ያለ ምንዳ ታሰጣለች፣ በፈጣሪ ዘንድ ክብር ታስገኛለች እና ሁሉም ከፈጣሪው ዘንድ ከፍ ያለውን ምንዳ ለማግኘት ይፋጠናል፡፡

ረመዷን አንድነት የሚሰበክበት፣ ሥነ ምግባር የሚነገርበት፣ እዝነት የሚደረግበት፣ ፍቅር የሚጎመራበት፣ መተሳሰብ ከፍ ከፍ የሚልበት፣ መተዛዘን የሚበረታበት ነው፡፡ በረመዷን ወቅት የተጣሉት ይታረቃሉ፣ ቂም የያዙት ቂማቸውን ስለ ፈጣሪ ፍቅር ብለው ይሽራሉ፤ በፍቅር ተቃቅፈው በሶላት ይበረታሉ፤ ቂም እና በቀልን እርግፍ አድርገው ይተዋሉ፤ በመካከላቸው አንድነትን እና ፍቅር ያነግሣሉ፡፡

በደሴ የአረብ ገንዳ መስጅድ ኮሚቴ ሊቀመንበር እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች የሐጂ እና ዑምራ ተጠሪ ዑስታዝ መሐመድ ሸሪፍ ረመዷን ከ12 ወራት ሁሉ በፈጣሪ ዘንድ የተመረጠው ወር ነው፤ በረመዷን ወር የሰውን ልጅ የሚያሳስተው ሰይጣን የሚታሰርበት፣ የሰው ልጆች ከሰይጣን ተንኮል ርቀው ፈጣሪያቸውን የሚያስቡበት ነው ይላሉ፡፡ ፈጣሪ በረመዷን ወር ሰይጣንን አስረዋለሁ ብሏል፤ ለመታሰሩም ምክንያት ሰዎች በረመዷን ወቅት መልካም ነገር ያደርጋሉ፤ ከሰይጣን ተጽዕኖ ይርቃሉ ነው የሚሉት፡፡

የሰው ልጅ ሲጠግብ ስጋዊ ፍላጎቱ እያየለበት ወደ ሌላ ነገር ይገባል፤ ያልተገባ ነገርም ያስባል፤ ሲራብ ግን ለዘመናት የተራቡትን ያስባል፤ ረሃብን ይረዳል፤ በጾም ብቻ ሳይኾን በማጣት የተራቡትን ያስባል፤ በጾም ወቅት ሰብዓዊነት ይልቃል፤ ሩህሩህነት ይፈጠራል፤ ማዘኑ እየዳበረ ይሄዳል፤ ሙስሊሞች በረመዷን ወቅት እየጾሙ ፈጣሪያቸውን ያስባሉ መልካም ነገርም ያደርጋሉ ነው የሚሉት፡፡

በረመዷን የሚፈጸሙ መልካም ነገሮች በአሏህ ዘንድ ከሌሎች ወራት ከሚሠሩት ሥራዎች እጥፍ ዋጋ አላቸውም ይላሉ፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዷን ወቅት ጀነትን እያሰበ መልካም ነገር ያደርጋል፤ በረመዷን ወቅት ሰው ከሰው የሚጠያየቅበት፣ የሰው ልጅ አቅጣጫ በአጠቃላይ ወደ በጎነት የሚሄድበት ነው ይላሉ ዑስታዝ፡፡

በረመዷን ወቅት ሰይጣን ይታሰራልና፤ የሰውን ልጅ የሚገፋፋው ኃይል ይቀንስለታል፤ ስጋም በጾም ይደክማልና ወደ መንፈሳዊነት ይቀርባል፤ መንፈሳዊነት ደግሞ በጎነትን ያሳስባል፤ ረመዷን ለሙስሊሞች ታላቅ ወር ነው፤ ከበጎ ነገሮች ጋር የሚገናኙበት ነው፡፡ በረመዷን ወቅት ያስከፋ፣ ያስቀየመ ሰው እንኳን ቢኖር ይቅር የሚባልበት፣ ማንንም ሳይለያዩ የሚወዱበት፣ የአምላክን ትዕዛዝ የሚያከብሩበት ነው፡፡

የረመዷን ወር የሚያልፈው ሶላት ሲሰገድበት፣ ቁርዓን ሲቀራበት፣ እዝነት ሲደረግበት፣ የተራበ ሲመገብበት፣ የተጠማ ሲጠጣበት፣ ይቅር ሲባባሉበት ነውና ለሙስሊሞች ታላቅ ነገር ይገኝበታል፡፡ የሰው ልጅ የተፈጠረብትን ዓላማ እና ሃይማኖቱን ጠንቅቆ ሲያውቅ ልቡን ለመልካም ነገር ያስገዛል፤ በምክንያት እና ለዓላማ እንደተፈጠረ ባወቀ ጊዜ ደግ ነገርን ያደርጋል፡፡ ፈጣሪ ለሰዎች በጎ እንድናስብ፣ ቅን እንድንኾን፣ ጠብ እንዳናነሳ፣ መገዳደል እንዳይኖር፣ እንኳን ለሰዎች ለእንስሳት እና እጽዋት እንድንጨነቅ ያስተምራል ይላሉ፡፡ ሰላምን እንድናወርድ ያዝዛል፤ በእስልምና አስተምህሮ አንድን ሰው ያዳነ የዓለምን ሕዝብ እንደአዳነ ይቆጠራል፤ አንድን ሰው የገደለ የዓለምን ሕዝብ እንደገደለ ይቆጠራል ነው ያሉኝ፡፡ ማዳን ማለትም ተቸግሮ መድረስ፣ ታሞ ማስታከም፣ አጥቶ ሳለ መስጠት ሊኾንም ይችላል፡፡

እርስ በእርስ መገዳደልን ፈጣሪ አይወደውም፤ ወንድም ወንድሙን መግደል የተገባ አይደለም፤ ፈጣሪ አያዝዘውም፣ የሚወደውም ሰላምና ፍቅር ነው፡፡ ግጭት የተፈጠረው፣ ሰላም የታጣው ወደ ልቡናቸውን ስላልተመለስን፣ ሰው ወደ ልቡናው ሲመለስ ወንድሙን አይገድልም፤ ወደ ልቡናችን እንመለስ፣ የበደለውን ይቅር ብለን፤ ሰላምን ለማምጣት ጥሩ አጋጣሚ ላይ ነን፤ በጾም ወቅት ሁሉንም ለማስተካል እድሎች አሉን፤ የሚያዋጣን ሰላም እና ፍቅር ነው፤ ሃይማኖት የሚያስተምረው ሀገር እንድንጠብቅ፤ ሃይማኖት ሳንለይ ለተቸገረ እንድንደርስ፣ ለራበው እንድናበላ፤ ሰላምን እና ፍቅርን ስናወርድ ፈጣሪም በእዝነት ዓይኑ ያየናል ነው ያሉት፡፡

የሰውን ልጅ ከምድራዊ ይልቅ ሰማያዊ ሕግ ይገዛዋል፤ ከዓለማዊ ይልቅ መንፈሳዊ ሕግ ያቅበዋል፤ ዓለማዊ ሕግ ግፋ ቢል ያስራል፤ ከጠና ይገድላል፤ ሰማያዊ ሕግ ግን ከሞት በኋላ ያለው ፍርድ ይከብዳል፤ ከሞት በኋላ ያለው ጥያቄ ይከብዳል፤ ከሞት በኋላ ያለው መጠየቅ፤ ከፈጣሪ ፊት በቀረበ ጊዜ የሚኖረውን ባሰብን ጊዜ ደግ ነገርን ብቻ እናደርጋለን፤ ሰዎች አስፈሪውን ነገር ባሰቡ ጊዜ ከመጥፎ ነገር ይከለላሉ፤ የበደላቸውን ይቅር ይላሉ ነው የሚሉት፡፡

ከምድራዊ ሕግ፣ ከመንግሥት በላይ የሚጠይቀን ፈጣሪ መኖሩን መዘንጋታችን ለግጭት ዳርጎናል፤ ሰላም እንድናጣ አድርጎናል፤ እርሱን ባሰብን ጊዜ ጥል እና ጥላቻን እርግፍ አድርገን ትተን መልካሙን ብቻ እናስባለን ነው ያሉት፡፡ አማኞች ሃይማኖታቸው የሚላቸውን ማሰብ አለባቸው፤ ሃይማኖታቸውን ባሰቡ ጊዜ ፈጣሪ የሚወደውን ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡ ሁልጊዜም ፈጣሪን ባሰብን ቁጥር ደግ ደጉን ብቻ እናደርጋለን፤ ለሰው ልጅ ትልቁ ማቀቢያው እና ማሰሪያው ሃይማኖቱን ሲያውቅ ነውም ይላሉ፡፡ የትኛውም ሃይማኖት መጥፎ ነገርን አይመክርም፤ ሰው ግደል፣ በድል አይልም፤ ስለዚህ ለምንድን ነው የምንገዳደለው? ለምንድን ነው የምንጨካከነው? እያልን ራሳችን መጠየቅ አለብን፤ መገዳደል ሃይማኖትን ካለማወቅ እና በሚገባ ካለመገንዘብ ይመጣል ነው የሚሉት፡፡

የሃይማኖት አባቶችም ትክክለኛ አስተማሪዎች፣ ትክክለኛ አባቶች ሲኾኑ አማኞችን ይጠብቃሉ፤ ያስተካክላሉ፤ እነርሱ ባልተገባ ነገር በተገኙ ጊዜ ግን ስለ ሃይማኖቱ ያለው ግንዛቤ ይወርዳል ነው ያሉት፡፡ ሁልጊዜም መልካምነትን ማሳብ፣ እዝነትን ማድረግ ለሀገር ሰላም ያመጣል፤ በፈጣሪ ዘንድም ዋጋን ያሰጣል ነው ያሉት፡፡

አምላክ ሃብትን የሚሰጥ ሌሎችን እንዲረዱበት ነው፤ ያለዚያ የሰጠሁህን የት አደረስከው? የሚል ጥያቄ አለ ይላሉ፡፡ ለሁሉም ነገር ሃይማኖቱን እና የሚያዝዘውን መረዳት ይበጃል ብለዋል፡፡ ሙስሊሞች በረመዷን ያሳለፉትን መልካም ነገር በሌላውም ጊዜ ማስቀጠል ይገባቸዋል፤ ስለምን ቢሉ ከምንዳ ላይ ምንዳ ይጨመርላቸዋልና ነው የሚሉት፡፡ መልካምነትን አድርጉ፣ ርህራሄንም አትዘንጉ፣ በጎነትን ሁልጊዜም አድርጉ፤ ያን ጊዜ ፈጣሪም ይደሰታል፤ ምድርም ትባረካለች፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም መጠናቀቁን ገለጸ፡፡
Next articleየዒድ አልፈጥር በዓል ገጽታ በዓለም ዙሪያ