
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መካ የሙስሊሞች ቅድስት ከተማ ናት። ካዕባ በመባል የሚታወቀው የአሏህ ቤት(መስጅድ) የሚገኘውም በዚች ቅድስት ከተማ ነው። መካ በሕዝበ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ “የዓለም ዕምብርት” በመባልም ትጠራለች።
የካዕባ መስጅድ ዓለሃረም ያለበት ቦታ ነው። በዚህ ክልል ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል የሠራ ሰው ድርብ ቅጣት ይጠብቀዋል። በቃ! ሐራም ነው።
እንስሳትን ማደን፣ ነፍስ መግደል እና ዛፍ መቁረጥም ፈጽሞ የተከለከለ ነው። በመካ በሚገኘው መስጅድ መስገድ በሌሎች መስጅዶች ከሚደረግ ሶላት በአንድ መቶ ሺህ ጊዜ ይበልጣል። ሰዎች በዓለም ዙሪያ ለሐጅ እና ዑምራ ወደ መካ ይጎርፋሉ፤ ምክንያቱም ካዕበቱል ሙሸረፋ ወይም ሃረም በመባል የሚታወቅ የአሏህ ቤት መኾኑን ያምናሉና።
በቅዱስ ቁርዓን መጽሐፍ ዘንድ ይህ የአሏህ ቤት በኢብራሂም እና በልጃቸው እስማኤል የተገነባ ነው ተብሎ በአማኙ ማኅበረሰብ ዘንድ ይታመናል። የረመዷን ጾም በዕምነቱ አስተምህሮ መሠረት ምዕምናን ፀባያቸውን የሚያንፁበት እና የሚያስተካክሉበት ታላቅ ወር ነው። በመኾኑም በረመዷን ከነፍስ ጋር የሚታገሉበት፣ ስሜትን ከሰይጣን ጉትጎታ የሚከላከሉበት ነው ተብሎ ይቆጠራል።
ሰው ሰውን የሚጎዳበትን ኃይለኛነቱን ዋጥ አድርጎ፣ ትዕግሥት ወደ ተላበሰ ሕይወት የሚመለስበት፣ ሥርዓት እና ደንብ የሚማርበት፣ በልብ ውስጥ እዝነት እና ሩህሩህነት የሚጸድቅበት፣ እርስ በእርስ በመተዛዘን የሚተሳሰርበት ብሎም የሚረዳዳበት ታላቅ ወር ነው ረመዷን። በረመዷን ጾም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከስግብግብነት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከምቀኝነት፣ ከተንኮል፣ ከጠብ አጫሪነት፣ ከመዝረፍ እና ከሌሎች ፀያፍ ተግባራት ራሱን በማንጻት ለፈጣሪ ራሱን ያስገዛል፡፡ ረመዷን አሏህን የመፍራት ወር በመኾኑ ምዕመኑ 11 ወራት ሙሉ ስሜቱን እና መጥፎ ምኞቱን ተከትሎ ለኖረ ሰው ሁሉ ልጓም፣ ለመልካም ሠሪዎች በረካ ሲኾን አዲስ የለውጥ ቤዛም የሚበሰርበት ነው።
ታዲያ የረመዷንን ጾም ጾም የሚያደርገው የምግብ እና የመጠጥ ተዓቅቦ ብቻ አይደለም። አሏህ የከለከላቸውን ነገሮች ሁሉ በመከልከል ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ በመታዘዝ መልካም ነገሮችን መሥራት የረመዷን ግዴታ ነው።
በረመዷን ወር ከምዕመኑ ምን ይጠበቃል?
ልግሥና
በቡኻሪ እንደተዘገበው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በረመዷን ወር ከሌላው ጊዜ ይበልጥ በጣም ለጋሥ ይኾኑ ነበር። በዚህ እሳቤ መሠረት “በረመዷን ውስጥ ሶደቃም ይሁን ዘካ መስጠት ይገባል። ማጣት ሳያሳስብ በማንኛውም ጊዜ የኾነ ነገር መስጠት አካላዊ፣ መንፈሳዊ እንዲኹም ሕሊናዊ ሸክምን ያቀላል። መስጠት ገንዘብ ብቻ ሳይኾን መልካም ሥራም ጭምር ነው” ብለዋል።
ጾምን በትክክል በመጾም፣ ሶላትን በወቅቱ በመስገድ፣ የተራዊህ ሶላት በመስገድ እና ላለፉት ወንጀሎች ተውባ በማድረግ ከትልልቅ ወንጀሎች ከራቁ ዓመቱን ሙሉ የሠሯቸው ትንንሽ ወንጀሎችም በረመዷን ይማርላቸዋል።
መካ እና ረመዷን
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ከአምስቱ ማዕዘኖች አንዱ የኾነው እና ሙስሊሞች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ሐጅን ጉዞ እንዲያደርጉ በሚያዘው ትዕዛዝ መሠረት ሙስሊሞች በመካ ይሰባሰባሉ። የሐጅ ሥፍራው ደግሞ ታላቁ የመካ መስጂድ ነው።
ጉዞ ወደ ሐጅ
የሐጅ ጉዞ የሚከናወነው በወሩ ከስምንተኛው እስከ አስራ ሦስተኛው ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
የሐጅ ሥነ ሥርዓት
በዚህ የተቀደሰ ሥፍራ የመካ የሐጅ ተጓዥ ሙስሊሞች በነጭ አልባሳት ደምቀው ካዕባን በመዞር የጁምዓ ሶላትን በታላቁ መስጂድ ያካሄዳሉ። የታዋፍ (ካዕባን የመዞር) ሥነ ሥርዓት ለሐጅ ለተጓዙ ሙስሊሞች የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ነው።
ጀንበር ከወጣችበት ሰዓት አንስቶ በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ መካ አቅራቢያ ባለው “ሚና” በተሰኘው ቦታ ምዕመናን ሶስት ማዕዘን በኾነው እና ሰይጣንን በሚወክለው የኮንክሪት ግንብ ላይ ድንጋይ በመወርወር የሐጅ ተጓዦች የዒድ አልአድሃ በዓልን ሰይጣንን በመውገር ነው የሚያከብሩት። ይህም አብርሃም ልጁን እስማኤልን ሊሰዋ በተጓዘበት ወቅት ሰይጣን የአምላኩን ትዕዛዝ እንዳይቀበል ሦስት ጊዜ የተፈታተነውን ይወክላል። ሙስሊሙ ከሐጅ ጉዞ በኋላ የመልካም ማዕረግ ባለቤትም ይኾናል። መረጃው የዘምዘም ዶት ኮም ነው።
ዒድ ሙባረክ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!