“ጽንፈኛው የሕዝብ ጥያቄ ይዣለሁ የሚለው በሕዝብ ጉያ ለመደበቅ የሚጠቀምበት ስልት ነው” ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ

23

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎጃም ኮማንድፖስት ከፍተኛ አመራሮች ከፍኖተ ሰላም ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ የጎጃም ኮማንድፖስት ሠብሣቢ እና የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሠማ ትምህርት ቤት ላይ ቦምብ ወርውሮ ሕጻናትን የሚጨርስ፣ ድልድይ የሚያፈርስ፣ የአርሶ አደሩን በሬ የሚያርድ፣ የሕዝብ ገንዘብ እና ንብረት የሚዘርፍ ቡድን ለሕዝብ ሊያዝን አይችልም ብለዋል፡፡ የሕዝብን ጥያቄም ለመደበቂያነት እየተጠቀመበት እንጅ ሊመልስ እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡

ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ሁሉም ነዋሪ የሰፈሩን ብሎም የከተማውን ሰላም ለመጠበቅ ቆርጦ መነሳት አለበት ነው ያሉት፡፡ ጠላትን ጠላት ብሎ መፈረጅ እና ማውገዝ እንደሚገባም አብራርተዋል፤ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይል እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር አካባቢውን በአግባቡ መጠበቅ አለበት ነው ያሉት።

በዕብሪት ተነሳስቶ የግል ፍላጎቱን ለማሟላት የሕዝብን ጥያቄ እንደ ሽፋን እየተጠቀመ ሕዝብ የሚጨርስን ዘራፊ ቡድን ሕዝቡ ማስቆም እንዳለበትም ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተናግረዋል። በክልሉም ኾነ በፌዴራል መንግሥት የተጀመሩ የሕዝብ ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ ሕዝቡ የራሱን ሰላም መጠበቅ አለበት ለዚህም ኮማንድፖስቱ ሕግ የማስከበር ግዳጁን ይወጣል ብለዋል።

በውይቱ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት ነዋሪዎች ኮማንድ ፖስቱ የጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ ይቀጥል ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ከመከላከያ ጎን ኾኖ ድጋፍ በመስጠት የተጀመረውን ልማት ያስቀጥላልም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ችግሮችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ(ዶ.ር) ሰላም የሁሉም መሠረት በመኾኑ የፍኖተ ሰላም ነዋሪዎች የሕግ ማስከበር ሥራው የተሳካ እንዲኾን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ተዘግተው የነበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ስለመጀመራቸው ተናግረዋል። አገልግሎቱን የበለጠ ለማስቀጠል ሁሉም ለሰላም መትጋት ይገባዋል ብለዋል። በሕዝባዊ መድረኩ ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ ጀኔራል መኮንኖች እንዲሁም የሁሉም ጎጃም የዞን አመራሮች ተገኝተዋል። መረጃው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር ፈጣሪን በመማጸን እና ለሰላም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሊኾን ይገባል” ሼህ ወለላው ሰኢድ
Next article“የረመዷን ጾም ከምግብ እና ከመጠጥ ተዓቅቦ በላይም ነው”