የአፄ ፋሲል ግንብን ለማስተዋዎቅ በአረንጓዴ ብርሃን የማስዋብ ሥራ ተከናወነ።

166

የአፄ ፋሲል ግንብን በአረንጓዴ ብርሃን የማስዋ መርሃ ግብር ዛሬ ማምሻውን ተከናውኗል።

የአየርላንድ መንግሥት በየዓመቱ የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ቀን በማስመልከት ዛሬ በአፄ ፋሲለደስ ግቢ የአፄ ፋሲል ግንብን በአረንጓዴ መብራት የማስዋብ ስራ ተሰርቷል። ሥራው ቅርሱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ ያለመ ነው።

ዝግጅቱ የተከናወነውም በአየርላንድ መንግሥትና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ትብብር ነው።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው በአረንጓዴ መብራት ቅርስን የማስተዋወቅ ሥራ ከዚህ ቀደም በላሊበላ መካሄዱን አስታውሰዋል፤ የአየርላንድ መንግሥት በወደደው ቦታና ጊዜ ይህን ተግባር እንደሚያከናውንና ሥራውም ቅርሱን እንደሚያስተዋውቅ ተናግረዋል።

በቅርሱ ላይ መብራቱ ሲበራ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለመኖሩ ለጠየቅናቸው ጥያቄም “ምንም ዓይነት ችግር እንደማያመጣ አረጋግጠን ነው የፈቀድነው፤ የሚቆየውም ለአንድ ሌሊት ብቻ ነው” ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በሪሁን ካሣው (ኢንጅነር) ደግሞ የአፄ ፋሲል ግንብን በአረንጓዴ መብራት ማሳመሩ ቅርሱን ለማስተዋዎቅ ትልቅ ትርጉም እንዳለውና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

አፄ ፋሲል ግንብን በአረንጓዴ መብራት ማሳመሩ የተሻለ ውበት ለመስጠትና በቱሪዝሙ ላይ በጎ ሚና እንደሚኖረው የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የአየርላንድ ኢምባሲ የልማት ትብብር አታሼ አቶ ፓትሪክ ማክማነስ ናቸው። ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ

Previous article“ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ውብ መገለጫ እሴቶች ስላሉት የየራሱን መገለጫ እንደሚወድ ሁሉ የሌላውንም ማክበር አለበት” ምሁራን
Next articleበ2011 ዓ.ም ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ጠፍተዋል፡