“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር ፈጣሪን በመማጸን እና ለሰላም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሊኾን ይገባል” ሼህ ወለላው ሰኢድ

23

ደብረ ማርቆስ፡ ሚያዝያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 445ኛውን የዒድ አልፈጥር በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡ የዒድ አልፈጥር በዓል ታላቁ የረመዳን ፆም መገባደጃን ተከትሎ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚከበር በዓል ነው። 1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶች ተከብሯል ። የእምነቱ ተከታዮች በከተማዋ በሚገኘው ቢንአፊፍ መስጅድ በመሠባሠብ ነው በዓሉን ያከበሩት።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰኢድ “ዕለቱ በረመዷን ወር ጸሎታችንን ለአሏህ በማቅረብ እና መልካም በመሥራት ከፈጣሪ ምንዳ የምናገኝበት ነው” ብለዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በጋራ ሲያከብር በሀገሪቱ ያጋጠመው የሰላም እጦት መፍትሔ እንዲያገኝ ፈጣሪን በመማጸን እና ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሊኾን እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

አሚኮ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮችም ታላቁ የረመዳን ፆም በመልካም ሁኔታ ማለፉን ተናግረዋል። ለሰላም የድርሻቸውን በመወጣት ሃይማኖታዊ አስተምህሮው በሚያዝዘው እና በሚፈቅደው መሠረት ማሳለፋቸውን አስረድተዋል። በዓሉን በራሳቸው አቅም ማክበር የማይችሉ ወገኖችን በማገዝም እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል።

ረመዷን ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች አንዱ መኾኑን የገለጹት የደብረ ማርቆስ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጸሐፊ ሞሐመድ ሲራጅ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸውን በማገዝ እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡ የአንድ ሀገር ትልቁ ሃብቷ ሰው መኾኑን የጠቀሱት አቶ ሞሐመድ እንደሀገር ያጋጠመው የሰላም እጦት እያስከተለ ያለው ሰብዓዊ ጥፋት እንዲቆም ሁሉም በአንድነት መቆም እና ችግሮችን በውይይት መፍታት አለበት ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡-ወንድወሰን ዋለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተከብሯል።
Next article“ጽንፈኛው የሕዝብ ጥያቄ ይዣለሁ የሚለው በሕዝብ ጉያ ለመደበቅ የሚጠቀምበት ስልት ነው” ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ