1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተከብሯል።

29

ደባርቅ: ሚያዝያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ30 ቀናት የረመዳን ጾም ሲጠናቀቅ የሚከበረው የዒድ አልፈጥር በዓል ዘንድሮ ለ1445ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ተከብሯል። የደባርቅ ከተማ የእምነቱ ተከታይ ነዋሪዎች ያለፉትን የጾም ቀናት በስግደት፣ በመርዳዳት፣ በመተሳሰብና ወደ ፈጣሪ የሚያቀርባቸውን ተግባር በመፈጸም ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

የዒድ አልፈጥር በዓል የደስታ በዓል ነው ያሉት የእምነቱ ተከታዮች በዓሉንም በጾም ወቅት እንዳደረግነው ኹሉ በመተሳሰብና በአብሮነት እናከብረዋለን ነው ያሉት። የደባርቅ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዳውድ ቡሽራ ከእስልምና አምስቱ ትእዛዛት ውስጥ አንዱ የሮመዳን ጾም ነው። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጾሙን ሶላት በመስገድ፣ ዘካተል ፊጥር በማዋጣት የተቸገሩና ለጾም መግደፊያ ለሌላቸው ወገኖች ዘካ በመስጠትና በመተሳሰብ አሳልፎ ለዒድ አልፈጥር በዓል ደርሰናልም ብለዋል።

የደባርቅ ከተማ የእስልምና እና ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የመተሳሰብና የመረዳዳት የቆየ ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወጣቶች በበዓሉ ዋዜማ የመስገጃ ቦታውን የማጽዳት ሥራ መሥራታቸው ለዚህ ማሣያ ነው ብለዋል። ይህ የመተሳሰብ ልምድም ከበዓሉ በኋላም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ 1445ኛውን ዒድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር እንደ ከዚህቀደሙ ኹሉ የመተሳሰብና የመተዛዘን ሥነ ምግባሩን በማስቀጠል ሊኾን እንደሚገባ መክረዋል። የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አበባው አዛናው በበዓሉ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጾሙን በጎ ተግባር በማከናወን ማሳለፉን ገልጸዋል።

የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ሙስሊም ማኅበረሰብ ሀገሩን በመውደድ፤ የሀገር እድገትና ለውጥ የእኔ ለውጥ ነው፤ ከኹሉም በላይ የሀገር ሰላምና ልማት ይቀድማል በማለት ከአጠቃላይ የሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ለአካባቢው ሰላም መስፈን በመሥራቱ ምሥጋና ይገበዋል ነው ያሉት ከንቲባው።
በመጨረሻም ከንቲባው ለመላው የደባርቅና አካባቢው ነዋሪ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች መልካም በዓል እንዲኾን ተመኝተዋል።

ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሐጂና ዑምራን አከታትሉ”
Next article“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር ፈጣሪን በመማጸን እና ለሰላም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሊኾን ይገባል” ሼህ ወለላው ሰኢድ