“ሐጂና ዑምራን አከታትሉ”

26

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፈጣሪያቸውን እያሰቡ ከዓለም ዙሪያ ይጓዛሉ፤ በቀደመው ዘመን ገሚሶች በእግራቸው፣ የቻሉት በፈረሶቻቸው እና በግመሎቻቸው፣ በረሃውን እያቋረጡ፣ ውኃ ጥሙን እና ረሃቡን እየታገሱ ወደ ተቀደሰችው ስፍራ ይገሰግሳሉ፡፡ በዚያችም ሥፍራ በደረሱ ጊዜ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ያመሠግናሉ፤ ለእርሱ ተገዥነታቸውን፣ የእርሱም አገልጋይነታቸውን በትሕትና ይገልጣሉ፡፡

እንደዛሬው በሰማይ መብረር፣ በምድር መሸከርከር ሳይኖር ሙስሊሞች ድካሙን ታግሰው፣ ክብርን ለማግኘት ወደ ተቀደሰችው ወደ መካ ሲጓዙ ኖረዋል፡፡ በዚያች ሥፍራ ተገኝቶ የተወደደችውን ማድረግ ታላቅ ክብርን ታስገኛለችና፡፡ በዚያች ሥፍራ መገኘት፣ በዚያችም ስፍራ ሶላት መስገድ ታላቅ ሐጅር ታስገኛለች፡፡ የዓለም ሙስሊሞች ፈጣሪያቸውን እያሰቡ ወደ ተቀደሰችው ሥፍራ ወደ መካ ይጓዛሉ፤ የእስልምና ሃይማኖት በተመሠረተባት፣ ነብዩ መሐመድ ሃይማኖትን በሰበኩባት፣ ባጸኑባት፣ ከላካቸው ከአሏህ ትዕዛዛት በተቀበሉባት ሥፍራ መገኘት፣ በዚያችም ስፍራ ሃይማኖቱን መፈጸም ታላቅ ክብርን ታስገኛለች፡፡

በተቀደሰው የረመዷን ወር በተቀደሰችው ሥፍራ መገኘት መታደል ነው፤ ከምንዳ ላይ ምንዳን መጨመር ነው፤ ሙስሊሞች በረከትን ለማግኘት ዑምራን ያደርጋሉ፤ ዑምራ በሃይማኖት የተፈቀደች፣ ሙስሊሞች ያደርጓት ዘንድም የተወደደች ናት ይባላል፡፡ ሙስሊሞች በዘመናቸው በመካ ተገኝተው ዑምራ እና ሐጂ ማድረግን ይመኛሉ፤ ይናፍቃሉም፡፡

በደሴ የአረብ ገንዳ መስጊድ ኮሚቴ ሊቀመንበር እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች የሐጂ እና ዑምራ ተጠሪ ዑስታዝ መሐመድ ሸሪፍ ዑምራ ታላቅ ዋጋ የሚገኝበት ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡ የሚገኘው ሐጅር ከፍ ያለ ነው፤ በመካ በተቀደሰችው ስፍራ ሄዶ ዑምራ ያደረገ ሐጅሩ ከፍ ይልለታል ነው የሚሉት፡፡

ነብዩ መሐመድ በተወለዱበት፣ እስልምና በተመሠረተበት ሀገር የሚደረጉ ኢባዳዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ ናቸው፡፡ እነዚያን ለማግኘት ሙስሊሞች ዑምራን ያደርጋሉ፡፡ የሚገኘው ክብር እና ዋጋም ከፍ ያለ ነው፡፡ የዓለም ሙስሊሞች ሁሉ በአንድ ላይ የሚገናኙበት፣ ወንድማማችነት እህታማማችነት የሚፈጠርበት፣ አንድነት ከፍ የሚልበት ነው ይላሉ፡፡ ዑምራ ታላቅ ዋጋ ያለው፤ የሚበረታታ ሃይማኖቱም የሚያዝዘው ነው ይሏታል፡፡

ዑምራን በየትኛውም ጊዜ ማድረግ ይቻላል፡፡ በረመዷን ወቅት ሲደረግ ደግሞ ክብሩ ተደራራቢ ይኾናል፤ በረመዷን ወቅት ዑምራ የሚያደርግ ዋጋው እጥፍ ድርብ ይኾንለታል ነው የሚሉት፡፡ በደሴ የመስጊድ አል ፈትህ ኢማም ዑስታዝ ሰኢድ አሊ ዑምራ ዓመቱን ሙሉ አንድ ሰው መሥራት እንደሚችል፣ ገደብ እንደሌለው የሚያመላክት ስያሜ ያለው እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

ዑምራ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተከበረችው እና በተቀደሰችው ስፍራ በመካ ይደረጋል፡፡ በዚያች ስፍራ ዑምራን ማድረግ ታላቅ ምንዳን ያሰጣልና፡፡ ዑምራን አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ እና ለዚያ ነገር ራስን ማዘጋጀት፣ ካዕባውን ሰባት ጊዜ መዞር፤ ካዕባውን ዞሮ ከጨረሰ በኋላ ከሶፋ እና ከመረዋ ተራራዎች ሰባት ጊዜ መመላለስ፤ ጸጉሩን ማሳጠር ወይም መላጨት የዑምራ ግዴታዎች ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህን ማድረግ አራቱ የዑምራ መሠረቶች ናቸው፡፡

ዑምራ ሲያደርጉም የጌታየ ታዛዥ ነኝ፤ ትዕዛዝህን አከብራለሁ፤ ለአንተ ተቀናቃኝ የለህም፤ አምልኮቴን ለማንም አላደርግም፤ ከአንተ ውጭ ማንንም አላመልክም እያሉ ያዜማሉ ነው ያሉት፡፡ የፈጣሪ ብቸኝነትን፣ አምላክነቱን እያወጁ ዑምራ ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡ ዑምራ እና ሐጂ ማድረግ የተወደደ እንደኾነ አስቀድሞ ገና በሃይማኖቱ ተነግሯል፡፡

ዑምራን ከዓመት እስከ ዓመት ማድረግ ይቻላል፤ በረመዷን ወቅት ማድረግ ደግሞ የተለየ ክብር ያሰጣል፤ በረመዷን ወቅት ዑምራን ማድረግ ሐጂ እንደማድረግ ይቆጠራል ብለው ነብዩ መሐመድ መናገራቸውንም ነግረውናል፡፡ አንድ ዑምራ አድርጎ ሌላ ዑምራ መድገም በመካከል ያለውን ወንጀል ያብሳል፤ ሐጂና ዑምራን አከታትሉ፤ ደጋግማችሁ አድርጉ፤ እነርሱ ማለት ድህነትን እና ወንጀልን ያሰወግዳሉ፤ ወናፍ የብረት ዝገትን፣ የወርቅ እና የብርን አፈር እንደሚያስወግደው ሁሉ ዑምራ እና ሐጂም ወንጀልን ያስወግዳሉ በማለት ነብዩ መሐመድ ተናግረዋል ነው ያሉን፡፡

ነብዩ መሐመድ በረመዷን ወቅት የሚደረግ ዑምራ ከእኔ ጋር ሐጂ እንደማድረግ ነው ብለው ተናግረዋል፤ ለሙስሊሞችም በረመዷን ወቅት ዑምራ ማድረግ ከነብዩ መሐመድ ጋር ሐጂ እንደማደርግ ይቆጠርላቸዋል፤ ታላቅ ቦታም አለው ነው ያሉት፡፡ ሙስሊሞች በአንድ ቦታ ዑምራን ማድረጋቸው አንድነታቸውን ያሳያል፡፡ በዑምራ ሙስሊሞች ይሠባሠባሉ፤ አንድነትን እና ፍቅርን በማምጣት በኩልም ታላቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሁሉም ወደ ካዓባው ዞሮ ይሰግዳል፤ በዚህም በአንድነት ለአንድ አምላክ መገዛትን ያሳያል ነው የሚሉት፡፡ ሙስሊሞች በአንድነት አንድ አምላካቸውን ያመልካሉ፤ በአንድነትም ተሠባሥበው በፈጣሪያቸው ዘንድ የተወደደችውን ያደርጋሉ፡፡

ታላቁ ወር ተፈጽሟል፡፡ ሙስሊሞች በታላቁ ወር የተወደደውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ፈጽመው ዒድ አልፈጥርን እያከበሩ ነው፡፡ ይች ቀን ከቀናቱ መካከል የተለየች ናት፡፡ እጅግም ጓጉተው ይጠብቋታል፤ በደረሰችም ጊዜ በፍቅር፣ በእዝነት፣ በመስጠት፣ በመተሳሳብ ያከብሯታል፡፡ ቀኗ ደርሳለች፤ ሙስሊሞችም በደስታ እና በፍቅር እያከበሯት፣ ለፈጣሪያቸው ምሥጋና እያቀረቡ እያሰቧት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ነብያት ለሕዝባቸው እምነትን እንጅ ገንዘብን አያወርሱም” ኡስታዝ በድሩ ሁሴን
Next article1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተከብሯል።