“ነብያት ለሕዝባቸው እምነትን እንጅ ገንዘብን አያወርሱም” ኡስታዝ በድሩ ሁሴን

31

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የረመዷን ወር የእስልምና ሃይማኖት ከተገነባባቸው አምስት መሰረቶች አንዱ የኾነው ፆም የሚከወንበት እና ከሂጅራ 12ቱ ወራቶች 9ኛው ወር ተደርጎ ይወሰዳል። የረመዷን ወር ፈጣሪ የሙስሊሞች የሕይወታቸው መመሪያ የኾነውን ቅዱስ ቁርኣን በጅብሪል አማካኝነት ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ያወረደበት የተቀደሰ ወርም ነው፡፡

የእምነቱ ተከታዮች “ቅዱሱ ወር” እያሉ በሚጠሩት በዚህ ታላቅ ወር ከሥጋዊ ፍላጎታቸው ታቅበው በስግደት፣ ቁርዓን በመቅራት፣ ዘካ በመስጠት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም ፈጣሪያቸውን ይማጸናሉ። ኡዝታዝ በድሩ ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በረመዷን ፆም የእምነቱ ተከታዮች አላህን በመፍራት ከመጥፎ ነገር ራሳቸውን በማቀብ መልካም ነገር እንዲሠሩ ማድረግ እንደኾነም ገልጸውልናል።

የረመዷን ፆም የሃይማኖቱ ተከታዮች አሏህ የማይፈልገውን ነገር እንዲጸየፉ ውስጣዊ ባሕሪን መግሪያም መንገድ ነው። ውስጣዊ ባሕሪው የተገራ አማኝ ደግሞ ውጫዊ ባሕሪውን ከመጥፎ ነገር እንዲያርቅ እና መልካም ነገርን እንዲከውን ያደርገዋል። ውስጥን ማጽዳት ሲቻል እንደ ግለሰብ ብሎም እንደ ሀገር ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጎልበት ያግዛል።

“በረመዷን ፆም የተፈቀደ ነገር የተከለከለ ነው። በረመዷን ወር የተፈቀደውን የተከለከለ የእምነቱ ተከታይ ከረመዷን በኋላ ያልተፈቀደለትን ነገር መዳፈር ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባሩ አይፈቅድለትም” ብለዋል ኡስታዝ በድሩ። ለተቸገሩት ዘካ መስጠት እና አቅመ ደካሞችን መርዳት ደግሞ ሌላኛው ሃይማኖታዊ መሠረት መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ የነብዩ ሙሐመድን ልግስና በማሳያነት ጠቅሰዋል። ነብዩ ሙሐመድ ምጽዋት ለምንዱባን ስለሚያከፋፍሉ ከሦስት ቀን በላይ ገንዘብ እንደማያስቀምጡ ነው የገለጹት። ነብዩ ሙሐመድ በረመዷን ልግስናቸው የተለየ እንደነበር ያነሱት ኡስታዝ በድሩ “ነብያት ለሕዝባቸው እምነትን እንጅ ገንዘብን አያወርሱም” እንዳሉም ገልጸዋል።

በረመዷን የሚከናወኑ መልካም ሃይማኖታዊ እሴቶች እና አስተምህሮዎች ሁሉ ከረመዷን በኋላ ባሉት 11 ወራትም አማኞች ራሳቸውን ለመግዛት፣ ለማነጽ እና ለማረቅ የሚተገብሩት በመኾኑ የረመዷን ወር በሙስሊሙ ልሂቃን እንደ ግብረ ገባዊ ማዕከል ተደርጎ እንደሚታይ ነው ኡስታዝ በድሩ የነገሩን።
በረመዷን በፆም በሶላት እና በስግደት ምህረትን እና ይቅርታን ከአላህ (ሱ.ዐ) ሲማጸን የቆየው ሕዝበ ሙስሊም በዒድ አልፈጥር የደስታ በዓል ደግሞ በአብሮነት፣ በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ በፍቅር በዓሉን ያከብራል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባሕር ዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት ተልዕኮውን በቁርጠኝነት በመወጣቱ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ችሏል” ጄኔራል አበባው ታደሰ
Next article“ሐጂና ዑምራን አከታትሉ”