
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር የክልሉ ሕዝብ እና ኮማንድ ፖስቱ በወሰደው የተቀናጀ እርምጃ አንፃራዊ ሰላምን ማምጣት መቻሉን የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገልጸዋል።
ጄኔራል አበባው ታደሰ ከሰሜን ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ መሪዎች እና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና ከወረዳ ኮማንድ ፖስት መሪዎች ጋር በአሁናዊ የጸጥታ ሁኔታ ዙሪያ እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የቀጣናው አሁናዊ የሰላም ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻልን አሳይቷል ያሉት ጄኔራል አበባው ታደሰ ጽንፈኛው ኀይል በተወሰደበት ጠንከር ያለ እርምጃ በአሁኑ ወቅት አቅሙን አጥቷል፣ በዚህም ምክንያት የሽፍታነት ባህሪን ለመላበስ ተገዷል ብለዋል።
ጄኔራል አበባው ታደሰ የባሕርዳር -ጎንደር ኮማንድ ፖስት በዘራፊው ቡድን ላይ በወሰደው እርምጃ እና በፈፀመው አኩሪ ገድል የጽንፈኛው ኀይል የኔትወርክ ትስስር ተበጣጥሷል ነው ያሉት፡፡ እርስ በራሱ ወደ መበላላት ደረጃ በመውረድ፣ ተስፋ በመቁረጥ ሕዝቡን የመዝረፍ፣ የማሰቃየት፣ የውንብድና እና የዘራፊነት ተግባር በመፈፀም ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በአማራ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ የዞን እና የወረዳ መሪዎች ኀላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ሊወጡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትሥስር ገጹ አስፍሯል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!