ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ያሳየውን የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የምዕራብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

16

ገንዳውኃ: ሚያዝያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 445ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በገንዳ ውኃ ከተማ ተከብሯል። የገንዳ ውኃ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ አህመድ ኑሬዬ”እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መተሳሰብና መደጋገፍ የዓላህ ትዕዛዝ ነውና ሕዝበ ሙስሊሙ ትዕዛዙን በመፈጸም የበረከቱ ተካፋይ መኾን ይገባዋል ብለዋል።

“በዓሉ ሲከበር ያለው ለሌለው አስቦና ደግፎ የሚውለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው፣ ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባትም ሆነ ወልዶ ማሳደግ የማይታሰብ በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ለሰላማችን ትልቅ ዋጋ መስጠት ይገባል” ብለዋል። የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ “መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እንዲኖር እና በከተማው እየተከናወኑ ባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እያደረገ ላለው ሁለንተናዊ ተሳትፎም አመስግነዋል። በመኾኑም ይህንን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል። ሕዝበ ሙሰሊሙ የአብሮነት እሴቱን በማጠናከር ለሀገሪቱ ሰላምና ልማት መረጋገጥ አበክሮ እንዲተጋም ጥሪ አቅርበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አባተ ነጋ ሕዝበ ሙስሊሙ የዘንድሮው የረመዳን የጾም ወቅት በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ማሳለፍ መቻሉን ጠቅሰዋል። በበዓሉ የታየውን የመደጋገፍ፣ መተባበር የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በልማቱ መድገም እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ድርቅ፣ ርሃብ፣ ግጭት፣ መፈናቀል እና ሞት እንዲወገድ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲረጋገጥ በረመዳን ሲደረገ የቆየው የጾም፣ የስግደት እና የሶላት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝበ ሙስሊሙ ለሰላም መጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
Next article“የባሕር ዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት ተልዕኮውን በቁርጠኝነት በመወጣቱ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ችሏል” ጄኔራል አበባው ታደሰ