
የ1 ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የተላለፈ መልዕክት፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሰላም መጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
የሕዝባችን ፍላጎት ሰላም እና ሰላም ብቻ ነው፡፡ በመርሕ እና እውነት፣ በሕግና እምነት የሚመራ የፍትሕ ሥርዓትን ማንበር ይፈልጋል፡፡ ይህንን ማረጋገጥ ደግሞ የፍትሕ ተቋማት በተለይም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተቋማዊ ሚና እንደኾነ እንረዳለን፡፡
በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሰላም እና ሰላማዊነት ቦታቸውን አጥተው ወንጀል እና ወንጀለኝነት በሕዝባችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እና ህይወት መስመር ሳንካ ኾነው ቆይተዋል፡፡ ይህንን አስወግዶ ሕዝቡን ከተደቀነበት ሰቆቃ ለማውጣት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና አባላት ከሰበአዊነት በተቀዳ ተቋማዊ መርሕ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም እና ፍትሕ እንዲሰፍን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሚሊሻ እና ከሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ጋር ስብራቶችን ለመጠገን በጀግንነት እና በመስዋዕትነት እየሠራን እንገኛለን፡፡
ተግዳሮቶቻችንን ቀርፈን የሕዝባችን ሰላም እንድናረጋግጥ የኅብረተሰቡ ትብብር እና አንድነት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ በመላው የክልላችን አካባቢ 1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ትብብር ላደረጉ ሁሉ ምሥጋናችንን እያቀረብን ኅብረተሰቡ በተለይም ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር ለሰላም መጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን፡፡
መላው የክልላችን ሕዝብ ሰላሙን ለመጠበቅ እና ለማጽናት በአርቆ አሳቢነት እና በአስተዋይነት አንድነቱን ጠብቆ ጸጥታውን እንዲያጸና፣ ከጥፋት መንገድ የራቀ ሁሉንም የሚጠቅም የሰላም መንገድን እንዲከተል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ አጋጣሚ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
እንኳን ለ1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!
ዒድ ሙባረክ
በጀግንነት መጠበቅ- በሰበዓዊነት ማገልገል!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን
ሚያዚያ/2016 ዓ.ም- ባሕርዳር