
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የቀድሞ ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሙለቀን መለሰ በሚኖርበት ሀገረ አሜሪካ ነው ሕይወቱ ያለፈው። ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን ያደረገው ሙሉቀን መለሰ የሙዚቃውን ዓለም በመተው በመንፈሳዊ የሙዝሙር ሥራዎች ውስጥ ያሳልፍ እንደነበር ይታወሳል።
ሙሉቀን መለሰ በጎጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም እንደ ተወለደ ግለ ታሪኩ ያወሳል። 10 ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ አዲስ አበባ ይኖሩ ከነበሩ አጎቱ ጋር እንዲማር ብለው የወሰዱት ሙሉቀን መለሰ ኮልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ሊገባ ችሏል።
ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር የነበረው ድምፃዊው እርሱ በነበረበት አካባቢ በተከፈተው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ በአቶ ተፈራ አቡነ ወልድ አማካይነት ለስድስት ወራት የዘለቀ የትምህርት እገዛ አግኝቷል። ገና የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለ ሙዚቃን የጀመረው ድምፃዊው በ1958 ዓ.ም በፈጣን ኦርኬስትራ ውስጥ ተቀላቅሎ በመግባት ለሁለት ዓመታት ያህል መሥራት ችሏል።
ከዚያ በማስከተል በ1960 ዓ.ም ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ ክፍል በመግባት ይበልጥ በሙዚቃ ሥራው ዝናን ማትረፍ ችሎ ነበር። በ1972 ዓ.ም ላይ ደግሞ ከዳህላክ ባንድ ጋር ተቀላቅሎ ሠርቷል፡፡ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በነበሩት ዓመታት እጅግ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎችንም መሥራት ችሏል። የአንጋፋዋ ሁለገብ ከያኒት የዓለምፀሐይ ወዳጆ እና የተስፋዬ ለሜሳን ግጥም እና ዜማዎች አቀንቅኗል።
ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ራሱን ከሙዚቃው ዓለም እስካገለለበት ጊዜ ድረስ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ለትውልድ አበርክቷል። በተለይ ባሕላዊ ጨዋታዎችን በዘመናዊ ለዛ በመጫወት ይታወቃል። ከ1980ዎቹ በኃላ ፊቱን ወደ መንፈሳዊ ሥራዎች በማዞር የመዝሙር ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ድረስ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን አድርጎ እንደቆየ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአንጋፋው ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ይገልጻል። ለቤተሰቦቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!