1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በኮምቦልቻ ከተማ ተከብሯል፡፡

21

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማዋ የዒድ ሶላት ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ ተጠናቋል። አሚኮ ያነጋገራቸው የኮምቦልቻ ከተማ ሙስሊሞች የረመዷን ወር በጥሩ መልኩ ማለፉን ገልጸው እስላማዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ሰላም እና እድገት የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
የዒድ ሶላት ከመጀመሩ በፊት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ሕዝበ ሙስሊሙ እምነቱ የሚያዘውን ሥነ ምግባር ማንጸባረቅ ይጠበቅበታል ብለዋል። የኢንዱስትሪ ከተማ ለኾነችው ኮምቦልቻ ከተማም ኾነ ለሀገራችን ሰላም፣ ልማት እና እድገት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ አሕመድ አወል በበኩላቸው ሙስሊሞች በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እና ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በመደገፍ በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“በዓሉ በሰላም የተከበረው ሀገር ሰላም በመኾኑ ነውና እንደ ሕዝበ ሙስሊሙ ለከተማችን ሰላም ዘብ ልንቆም ይገባል” ብለዋል፡፡ ሼህ አወል በመጨረሻም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች “እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካባቢን ሰላም እና ደኅንነት በመጠበቅ ሕዝበ ሙስሊሙ የድርሻውን አንዲወጣ ተጠየቀ፡፡
Next articleየቀድሞው ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።