“ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ውብ መገለጫ እሴቶች ስላሉት የየራሱን መገለጫ እንደሚወድ ሁሉ የሌላውንም ማክበር አለበት” ምሁራን

211

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት ለአንድነት እንጂ ለልዩነት ምክንያት መሆን እንደሌለባቸው ምሁራን መክረዋል፡፡

ሰባተኛው ዓለም አቀፍ የቋንቋ፣ የባህል፣ የተግባቦት እና የማንነት መድረክ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ የሚገኘው መድረክ ዋና ዓላማ በቋንቋ፣ በባህል፣ በተግባቦት እና በማንነት ላይ የተደረጉ የጥናት ውጤቶችን ማስፋት እና በማስተማሪያነት መጠቀም ነው፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲ ፋኩልቲ ዲን ሠፋ መካ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት ደግሞ ምክክሩ በጥናት የተለዩት ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ዛሬ የቀረቡት የጥናት ውጤቶችም ተማሪዎችም ሆነ መምህራን ዕውቀት የሚያገኙባቸው፣ የማጣቀሻ እና የመማሪያ ግብአት ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን ረዳት ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡

“በሰባተኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት ላይ ትኩረት አድርገን እየተወያየንበት የምንገኘው ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ነው፤ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ካለን ልዩነት በበለጠ አንድ የሚያደርጉን እሴቶች ይበዛሉ፤ እነዚህም ያሉብንን ችግሮች በብስለት እና በውይይት እንድንፈታ በር ይከፍታሉ” ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ሠፋ መካ፡፡ የባህል እና የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ በምን መልኩ መመለስ እንዳለባቸው፣ ሊነሱ የሚገባቸው ሀሳቦች እና የቃላት አጠቃቀምን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማካተት ጥናቶቹ ስለቀረቡ ጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ከጅግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡት መምህር ዓሊኑር አህመድ “ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት እኛን የሚያለያዩ ሳይሆኑ አንድ ሊያደርጉን ይገባል፡፡ ቋንቋችን እና ባህላችን መገለጫችን ስለሆኑ በሀገራችን እየተዘዋወርን እንዳንሠራ እና እናዳንኖር ማድረግ የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዜጎች በማንነታቸው ሲጎዱ በማየቴ እጅግ አዝኛለሁ” ብለዋል፡፡

ቋንቋ እና ባህልን አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሣን ዝግጅት ትምህርት ክፍል መምህር ዘላለም ልየው በበኩላቸው “ማንኛውም ማኅበረሰብ የራሱ ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት አለው፤ ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ውብ መገለጫ እሴቶች ስላሉት የየራሱን መገለጫ እንደሚወድ ሁሉ የሌላውንም ማክበር አለበት” ብለዋል፡፡

አንዱ የአንዱን ባህል እና ቋንቋ ማድነቅ እና ማክበር አለበት ያሉት መምህሩ የማኅበረሰቡም አመለካከት በዚህ መልኩ መገራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እሴቶች ከልዩነት ይልቅ ተመሳሳይነት እንዳላቸውም ጥናትን መሠረት አድርገው መስክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleቺርቤዋ-30-6-2012
Next articleየአፄ ፋሲል ግንብን ለማስተዋዎቅ በአረንጓዴ ብርሃን የማስዋብ ሥራ ተከናወነ።