
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ አሥተዳደር በእምነቱ ተከታዮች በተለያዩ ሥርዓቶች ነው እየተከበረ የሚገኘው። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የመደጋገፍ የመተሳሰብ እና የአብሮነት መገለጫ የኾነው የዒድ አልፈጥር በዓል በሁመራ ከተማ ተከብሯል። የእምነቱ ተከታዮች በሶላት፣ በመንዙማ እና በተለያዩ ሥርዓቶች እያከበሩትም ነው።
የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳይ ሊቀ መንበር ሼህ ነጋ ማርኮ “የዒድ አልፈጥር በዓል የተቸገሩትን የምንረዳበት፣ የተራቡትን የምናበላበት፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል ነው” ብለዋል። በዓሉ ሲከበር የአሏህን ትዕዛዝ በመጠበቅ የታሰሩትን በመጠየቅ የተራቡትን በማብላት የተጠሙትን በማጠጣት ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸውን አዛውንቶች በመደገፍ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
“ለሀገራችሁ ሰላም እና ለሕዝቦች በአንድነት ለአምላካችሁ ስትጸልዩ እና ስታመሠግኑ ቆይታችኃል” ያሉት የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አለሙ አየነው ናቸው ። በዓሉ ሲከበር ከሌሎች የሃይማኖት ተከታይ ወንድሞች ጋር በአብሮነት እና በፍጹም ፍቅር በመደጋገፍ ሊኾን እንደሚገባም አስረድተዋል።
የዞኑ አንጻራዊ ሰላም የተጠበቀ እንዲኾን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የመረዳዳት የመተባበር እና እርስ በእርስ የመከባበር ተምሳሌት የኾነው የዒድ አልፈጥር በዓል ውስጣዊ አንድነት የሚጠናከርበት፣ ሰላም እና ፍቅር የሚጸናበት በዓል ነው ብለዋል። የተቸገሩትን መረዳት እና መደገፍ በጾም ጊዜ ብቻ ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ በመደገፍ ለወገኖች ደጀን መኾን እንደሚገባም አስረድተዋል።
የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሰላም ወዳድ እና የሰላም አርዓያ በመኾኑ የሀገሪቱም ይሁን የአካባቢው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን የበኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣም አስገንዝበዋል። የሀገሪቱ ሰላም የሚጸናው በሃይማኖቶች መካከል መከባበር እና ፍቅር ሲኖር በመኾኑ አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር የሀገርን አንድነት ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
የእምነቱ አባቶች ለእምነቱ ተከታዮች በጎነትን ፍቅርን እና መረዳዳትን በማስተማር እንዲሁም በተግባር እንዲገልጹት በማድረግ ቀጣዩ ትውልድ የሀገርን ሉዓላዊነት እንዲያስከብር የአባትነታችሁን ኀላፊነት ልትወጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው በዓሉን በመከባበር እና በመረዳዳት በአብሮነት እያሳለፉ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!