
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አልፈጥር በዓል በባሕር ዳር ከተማ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማ አሥተዳደሩ ከዚህ በፊት ለሕዝበ ሙስሊሙ የሰጠውን ቦታ ምቹ በማድረግ በዓሉ በዚያ የሚከበርበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንሠራለን ብለዋል፡፡
የረመዷን ወር በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በፍቅር፣ በናፍቆት፣ በጉጉት፣ የሚጠበቅ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በጾም፣ በኢባዳ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚቀራረቡበት፣ በጎነት አብዝቶ የሚከናወንበት፣ ምህረት እና ይቅርታ የሚፈጸምበት ወር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የከተማዋ ሙስሊሞች ሃይማኖቱ የሚያዝዘው እና በረመዷን ወቅት የሚፈጸሙ መልካም ተግባሮች መፈጸማቸውንም ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮውን የዒድ አልፈጥር በዓል የምናከብረው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ውስጥ ኾነን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በበዓሉ ዋዜማ ሰግደው በሚመለሱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ ግድያ መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት በዓሉን በሃዘን ውስጥ ኾነን እንድናከብረው አስገድዶናል ነው ያሉት፡፡
አረመኔያዊ የኾነው የሽብር ድርጊት ሰው ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ዘግናኝ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ድርጊቱን በጽኑ እንደሚያወግዘውም ገልጸዋል፡፡ የሽብር ጥቃቱ ዋና ዓላማ ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ወንድሞቹ ጋር ወደ ግጭት እንዲገባ፣ ከተማውን፣ ክልሉን የወድመት እና የእልቂት ቦታ ለማድረግ፣ ክልል እና ሀገርን ለማፍረስ የወጠኑት ነው ብለዋል፡፡
ተግባሩ ተንኮላቸውን ለማሳካት ያሰቡት እንደነበርም አንስተዋል፡፡ አርቆ አሳቢው፣ ሰላም ወዳዱ የከተማዋ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በአግባቡ መዝኖ፣ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ፣ በአስተውሎት ተመልክቶ፣ ሽብር ፈጻሚ ሽብርተኞች በሕግ እንዲዳኙ እንጂ ሌላ አያስፈልግም በሚል ላደረገው አስተውሎት ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
ችግርን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ብልሃትን፣ ጥበብን፣ የሴረኞቹን እኩይ ተግባር ያከሸፈ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ንጹሃንን መግደል በመንግሥት እና በሌሎች አካላት በማሳበብ እነርሱ የሰላም ጠበቃ ለመምሰል የሚያደርጉት እኩይ ተግባር ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ የጥፋት ኃይሎች በሕግ ፊት ቀርበው ሕጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ተጋድሎ ክልሉ ከመፍረስ አደጋ ድኖ በየቀኑ የሚያድግ ሰላም መረጋገጡንም ተናግረዋል፡፡ የጥፋት ኃይሎች በከተማዋ እና በክልሉ ያልፈጸሙት በደል እና ያላደረሱት ጥፋት አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡
በጥፋት ኃይሎች ሰው እንደሚገደል፣ ንብረት እንደሚወድም፣ እንደሚዘረፍ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ቦምብ እንደሚፈነዳ፤ ሰው እንደሚታገትም ተናግረዋል፡፡ የጥፋት ኃይሎች ሽፋን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አማራን ማውደም ለአማራ ጥያቄ መልስ ሊኾን አይችልም ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በባለቤቱ በአማራ ሕዝብ፣ በአማራ ክልል መንግሥት፣ በፌዴራል መንግሥት እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ሰላማዊ ትግል የሚመለስ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ይፈታል የሚል ጽኑ አቋም አለውም ብለዋል፡፡ ከሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ጋር በመኾን ለሰላም እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ “እስላም ሰላም ነው፤ ለሰላም አብረን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሠራለን” ብለዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ በችግር ውስጥም ኾኖ የልማት ሥራዎችን እየከወነ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ያደሩ፣ የተጀመሩ እና አዳዲስ መንገዶችን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከ22 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ በከተማዋ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ጠላቶቻችን በሚያስቡት መንገድ ሳይኾን በላቀ መንገድ እየተጓዝን መኾናችንን ልንነግራቸው እንፈልጋለን ነው ያሉት ከንቲባው፡፡
የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም በትጋት እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ፡፡ በከተማዋ የከንቲባ ችሎት በማስጀመር ፍትሕን በአደባባይ መስጠት መጀመሩንም አንስተዋል፡፡ ለዓመታት መልስ ያላገኙ ጥያቄዎችን መመሰላቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እየለዩ እንደሚፈቱም ገልጸዋል፡፡ ሕግ እና አሠራርን በመጠበቅ ምላሽ እንሰጣለን ነው ያሉት፡፡
ሰላማችን ይመለሳል፣ ወደ ነበርንበት ቁመና እንመለሳን ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አማራ በአማራነቱ ቆሞ፣ ለሀገር ልማት እና ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ክፉውን ጊዜ ከመንግሥት ጋር በመኾን ሰላምን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓሉ የሰላም እና የፍቅር እንዲኾንም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!